ለእኛ የሚስማማውን የቆዳ መንከባከቢያ እንዴት መምረጥ እንችላለን?

የቆዳ ህክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ ቆዳችንን ለመንከባከብ የምንጠቀማቸው ምርቶች እንደየቆዳችን አይነት የአንዳችን ከአንዳችን የተለዩ የሚሆኑበት እድል ሰፊ ነው፡፡ ስለዚህ ሁሌም ቢሆን አንድን የቆዳ መንከባከቢያ ምርት ገዝተን ከመጠቀማችን በፊት ከእኛ ጋር በትክክል የሚስማማ መሆኑን አስቀድመን ማወቁ ቆዳችን ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያገኝ ከማስቻሉም በላይ ከተለያዩ የጎንዮሽ ጉዳቶች ይታደገናል፡፡

የቆዳ መንከባከቢያ ስንመርጥ የሚከተሉትን ቁልፍ ነገሮች እናስታውስ፤

ቆዳችንን እንወቅ

የቆዳ አይነት የቆዳ መንከባከቢያ ምርት ስንመርጥ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ ነገሮች መካከል አንዱና ዋናው ነው፡፡ በተለይ የሚያሳክክና የሚቆጣ ቆዳ ያላቸው ሰዎች በቆዳ መንከባከቢያ ምርቱ ውስጥ ስለተካተቱት ግብአቶች ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው፡፡ ይህም ሲባል ለምሳሌ፣ ወዛም የቆዳ አይነት በሌሎች የቆዳ አይነቶች ላይ መሰነጣጠቅና ማቃጠል የሚያስከትሉ የተለያዩ ግብአቶችን መቋቋም እንደሚችልም ልብ ይሏል፡፡

በግፊት አንግዛ

አንዳንድ ጊዜ የምርቶች የንግድ ስያሜ ትልቅ መሆኑ አልያም የምርት ማሸጊያዎች ማማር ምርቱን እንድንገዛ ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህ ስህተት ነው፡፡ ደግሞም ጓደኞቻችን ምርቱን ስለተጠቀሙት አልያም ስለወደዱት እኛም መግዛትና መጠቀም አለብን ብለን ማሰብ የለብንም፤ ይልቁንስ የእነርሱ የቆዳ አይነት ምን እንደሆነ እንዲሁም ምርቱን ሲጠቀሙ ቆዳቸው ላይ የሚስተዋሉትን አወንታዊና አሉታዊ ለውጦችን በሚገባ ለይተን ማወቁ ምርቱ ለእኛ ተስማሚ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ ያስችለናል፡፡

ሽታን/መዓዛን እናስወግድ

እንግዲህ የቆዳ መንከባከቢያ ስንገዛ ከግብአቶቹ መካከል መዓዛ የሚፈጥሩ ንጥረ ነገሮች እንዳይካተቱ የሚመከርበት ዋነኛው ምክንያት እነዚህ ሽታ አልያም መዓዛዎች የቆዳ አለርጂ አልያም መቆጣት የማስከተል እድላቸው ከፍ ያለ ስለሆነ ነው፡፡ በተለይ በቶሎ የሚቆጣ ቆዳ ያላቸው ሰዎች ሽታ ያላቸውን የቆዳ መንከባከቢያዎች እንዳይጠቀሙ ይመከራሉ፡፡

ተፈጥሮአዊ ነው ማለት የተሻለ ነው ማለት አይደለም

ሌላው እነዚህን የቆዳ መንከባከቢያዎች በምንመርጥበት ጊዜ የምናውቃቸው ተፈጥሮአዊ ግብአቶችን ስንመለከት ምርቱ ጥሩ ነው ብለን ልናስብ እንችላለን፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሌም ትክክል ላይሆን ይችላል፡፡ ምናልባትም እነዚህ ተፈጥሮአዊ ነገሮች ከእኛ ጋር የሚስማሙ ላይሆኑ ብሎም አለርጂክ ሊፈጥሩ ይችላሉና ቆም ብሎ መመርመር ብልህነት ነው፡፡

Celebrity News
Daily Feta Posts

Recent post

Daily Feta

Other Post