“ሚዲያዎች በዕውቀትና በሙያው ልምድ ባላቸው ሰዎች ቢመሩ ውጤታማ ይሆናሉ” ጋዜጠኛ መሰለ ገብረሕይወት

አዲስ አበባ፡- ሚዲያዎች በዘርፉ ዕውቀትና በሙያው ልምድ ባላቸው ሰዎች መመራት ከቻሉ ውጤታማ ይሆናሉ ሲል ጋዜጠኛ መሰለ ገብረሕይወት ተናገረ።

ጋዜጠኛ መሰለ ገብረሕይወት “የሚዲያ አመራር” የተሰኘው መጽሐፉን በሚመለከት ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረገው ቆይታ እንደገለፀው፤ የሚዲያ አመራሮች በሙያው ልምድና ዕውቀት ያላቸው ሊሆኑ ይገባል።

ሙያውን በአግባቡ የሚያውቁ አመራሮች ስለተቋሙ አሠራርና የመረጃ ሥርዓት በቂ ልምድ ይኖራቸዋል። ይህ ደግሞ መገናኛ ብዙኃኑን ውጤታማ እንዲሆኑና በተደራጀ መንገድ መረጃዎችን ለሕዝብ እንዲያደርሱ ያግዛል ብሏል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በሚታየው ነባራዊ ሁኔታ ሲታይ የሚዲያ አመራሮች ዘርፉን በሚገባቸው ልክ በማገልገል ላይ እንደማይገኙ የጠቆመው ጋዜጠኛ መሰለ፤ ይህም ሚዲያው በሚጠበቅበት መጠን ተፅዕኖ መፍጠር እንዳይችል ጋሬጣ ሆኖበታል ሲል ገልጿል።

ሚዲያዎችን በፖለቲካ ሹመኝነት ምደባ እንዲመሩ ከማድረግ ይልቅ ዘርፉን በአግባቡ በተረዱ ሰዎች እንዲመሩ ማድረግ ለሃገርም የሚጠቅም ለውጥ ለማምጣት ይረዳል። ሚዲያውን ውጤታማና ተጽዕኖ ፈጣሪ ለማድረግ ዕውቀት፤ ልምድና ክህሎት ላይ የተመሠረተ አካሄድን መከተል ይገባል ብሏል።

እንደ ጋዜጠኛ መሰለ ገለፃ፤ የሚዲያ አመራሮች የትምህርት ዝግጅት ሚዲያው ከሚፈልገው ጋር የማይያያዝና ዘርፉን የማያበረታታ መሆን የለበትም። በዚህ ረገድ ችግር ከተፈጠረ አጠቃላይ አሠራሩም እክል ያጋጥመዋል።

የሃገሪቱ የሚዲያዎች ችግር ዘርፈ ብዙ መሆኑን የተናገረው ጋዜጠኛ መሰለ፤ ሚዲያው ለሃገር ዕድገት ለሚኖረው ፖለቲካዊ፤ ማኅበራዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅዖ ከሚጠበቀው አንጻር እምብዛም መሆኑን ተናግሯል።

እንደ ጋዜጠኛ መሰለ ንግግር የሚዲያው ዘርፍ እንደ ኢንዱስትሪነቱ የሚገባውን ያህል ትኩረት እየተሰጠው አይደለም። ይህም ሳቢነት የሌለውና ጥራቱም የተጓደሉ ይዘት ያላቸው ዘገባዎችን በሰፊው እንዲስተዋሉ ምክንያት ሆኗል።

የመንግሥትን ሚዲያዎች ማየት ቢቻል የመንግሥትን ጥንካሬ ብቻ የሚያትቱና ለገዢው አካል እንደ አፍ በመሆን የሚያገለግሉ ዘገባዎችን ብቻ ሲዘግቡ፤ በተቃራኒው የግል መገናኛ ብዙኃንም የመንግሥትን ድካም ብቻ እየተከታተሉ መዘገባቸው ዘርፉን በእጅጉ እየጎዳ እንደሚገኝም ጋዜጠኛው ጠቁሟል።

ይህንንና መሰል ችግሮችን ለማረቅ በሚል በሚዲያ አመራርነት ላይ ያተኮረ መጽሐፍ ማዘጋጀቱን ገልጾ፤ መጽሐፉ የሚዲያ አመራሮች ክህሎት ምን መሆን አለበት? ሚዲያ ሙያዊ በሆነ መንገድ እንዴት ይመራል? አንድ የሚዲያ ተቋም ከሌላ ተቋማት ምን የተለየ መንገድ አለው የሚሉትና መሰል መሠረታዊ ጉዳዮችን እንደሚዳስስም ጋዜጠኛ መሰለ ገብረሕይወት ተናግሯል።

መጽሐፉን የረዥም ዓመት የሥራ ልምዱንና በትምህርት የቀሰመውን ዕውቀት በማዋሓድ ያዘጋጀው እንደሆነ የገለጸው ጋዜጠኛ መሰለ፤ መጽሐፉ በጋዜጠኝነት ትምህርት እንዲሁም በሚዲያ አመራር ዘርፍ ላይ የራሱ አስተዋጽዖ እንደሚኖረውም እምነቱ መሆኑን ተናግሯል።

የሚዲያ አመራር በሚል ርዕስ በጋዜጠኛ መሰለ ገብረሕይወት የተዘጋጀው መጽሐፍ ከትላንት በስቲያ ተመርቋል። መፅሐፉ 323 ገፆች ያሉት ሲሆን፤ በ13 ምዕራፎች ተሰንዷል።

Celebrity News
Daily Feta Posts

Recent post

Daily Feta

Other Post