ስላገረሸው ጦርነት እና ስለህወሓት የሰላም ጥሪ እስካሁን የምናውቀው

ሁለት ዓመት ሊሞላው አንድ ወር ገደማ የቀረው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነትት ባለፈው ነሐሴ 18/2014 ዓ. ዳግም መቀስቀሱ ለወራት የቆየው ተኩስ አቁም እንዲያበቃ ምክንያት ሆኗል።

ለጦርነቱ ዳግም መቀስቀስ ሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች እርስ በርሳቸው ይወቃቀሳሉ።

ከዚህ በፊት ተፋላሚ ወገኖቹ ለማሸማገል የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም እስከ አሁን ደም አፋሳሹን ጦርነት ለማስቆም የሚያስችል ውጤት ሳይገኝ ቀርቷል።

ባላፈው ሳምንት አሜሪካ አዘጋጀችው በተባለ የውይይት መድረክ የመንግሥትና የህወሓት የሰላም ተደራዳሪዎች ጂቡቲ ላይ ተገናኝተው መነጋገራቸውን ውስጥ አዋቂዎች ይጠቁማሉ።

የትግራይ ኃይሎች በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር በሚካሄደው የሰላም ድርድር ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውንና በድርድሩ የሚሳተፉ ተወካዮችን መሰየማቸውን ያሳወቁት ይህን ተከትሎ ሊሆን ይችላል የሚሉ መላ ምቶች አሉ።

ህወሓት ከዚህ ቀደም በአህጉራዊ ድርጅቱበ ላይ ሲያሰማ የነበረውን ትችት ትቶ፣ በአዲስ ዓመት የመጀመሪያ ዕለት መስከረም 01/2015 ዓ.ም. በወጣው መግለጫ በኅብረቱ በኩል ለሚደረገው ድርድር አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር የአስቸኳይ ተኩስ ማቆም ስምምነት እንዲደረግ ፍላጎት እንዳለው ገልጿል።

ግጭቱን ለማስቆም በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት የሰላም ድርድር ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው በተደጋጋሚ ሲገልጥ የቆየው የኢትዮጵያ መንግሥት ግን የትግራይ አመራሮች ላቀረቡት ሐሳብ እስካሁን የሰጠው ምላሽ የለም።

የአየር ጥቃት ክሶች

የህወሓት አመራሮች የእርስ በእርስ ጦርነቱ በንግግር ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸው ቢገልጡም የትግራይ ኃይሎች ዋና አዛዥ ጄኔራል ታደሰ ወረደ ጦርነቱ በተለያዩ ግንባሮች ተጠናክሮ መቀጠሉን ይናገራሉ።

አዛዡ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሠራዊት ባለፉት ቀናት በከፈተቱ መጠነ ሰፊ ጥቃት ሽራሮን ጨምሮ የተለያዩ የትግራይ አካባቢዎችን መያዛቸውን ገልጠዋል።

ጄኔራሉ አክለው ባለፉት አምስት ቀናት ያልተቋረጠ ከባድ የሚባል ጦርነት በተለያዩ ግንባሮች እየተካሄደ መሆኑን ተናግረው፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት ተከዜ ድልድይን ተሻግሮ ፀሊም ወየ ደርሶ ወደ ደደቢት ተቃርቧል ብለዋል።

ህወሓት፤ ባለፉት ሁለት ቀናት በትግራይ ክልል መዲና መቀለ መንግሥት የድሮን ጥቃት ፈፅሞ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል ሲል ይከሳል።

ማክሰኞ ዕለት ተፈፀመ የተባለው የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት የመቀለ ዩኒቨርሲቲ ዓዲ ሓቂ ካምፓስ እንዲሁም የህወሓት ንብረት በሆነው ድምጺ ወያኔ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ያነጣጠረ መሆኑ ተነግሯል።

ረቡዕ ደግሞ አምሳል ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በተፈጸመ ጥቃት 10 ሰዎች መሞታቸው እና ከ10 የሚበልጡ ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው የአይደር ሆስፒታል ሐኪሞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

መንግሥት በተከታታይ ቀናት ፈጽሞታል ለተባሉት የድሮን ጥቃቶች ክስ እስከ አሁን የሰጠው ምላሽ የለም።

በትግራይ ክልል ባለው የግንኙነት አገልግሎት መቋረጥ ምክንያት ደረሱ የተፈጸሙ የተባሉ ጥቃቶች እና የደረሱ ጉዳቶችን በገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልተቻለም።

የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ለቢቢሲ ኒውስ ዴይ በሰጡት ቃል የትግራይ ኃይሎች ከኢትዮጵያና ኤርትራ ሠራዊት ጋር እየተዋጉ መሆናቸው ገልጠው፣ በመቀለ ከተማ ተደጋጋሚ የድሮን ጥቃት እየተፈጸመ ነው ብለዋል።

“ቢሆንም ሰላም ስትራቴጂክ ምርጫችን ነው፤ አሁንም የፖለቲካ ችግር የሆነው ነገር በፖለቲካዊ መንገድ በውይይት ብቻ እንዲፈታ አጥብቀን እንጠይቃለን” ብለዋል።

ማን ምን አለ?

ምንም እንኳ ማዕከላዊው መንግሥት ህወሓት ላቀረበው “የሰላም ጥሪ” እስካሁን ይፋዊ ምላሽ ባይሰጥም አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት የትግራይ ኃይሎችን መግለጫ በጥርጣሬ ይመለከቱታል።

የሰላም ሚኒስቴር ዴኤታው አቶ ታዬ ደንደአ፤ “ስህተት መኖር የለበትም። በአንድ አገር አንድ የመከላከያ ሠራዊት ነው የሚኖረው፤ ይህ ዓለም አቀፍ መርኅ ነው። የሰላም ንግግር ከመጀመሩ በፊት የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ መፍታት አለባቸው” ሲሉ በትዊተር ገፃቸው ላይ ፅፈዋል።

ህወሓት በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር በሚካሄድ የሠላም ድርደር ሂደት ውስጥ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑን መለግጹን ተከትሎ አንዳንድ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች መግለጫ አውጥተዋል።

ከእነዚህ መካከል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ይገኙበታል።

ኢዜማ፤ “ዘላቂ ሠላም ማረጋገጥ የሚቻለው የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በምንም መልኩ ጥያቄ ውስጥ ሳይገባ ሊሆን ይገባል” ብሏል በመግለጫው።

አብን በበኩሉ “ህወሓት ድርድር እና ሰላማዊ የግጭት መፍቻ አማራጮችን በድጋሚ የጦርነት ማራመጃ እና የሽብር ማሳለጫ መሣሪያ አድርጎ እንዲጠቀም ሊፈቀድለት አይገባም” ብሏል በመግለጫው።

የአሜሪካ መንግሥት፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የአውሮፓ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤ የትግራይ ኃይሎች ተኩስ አቁመው ለመደራደር ዝግጁ መሆናቸውን መግለጻቸውን አዎንታዊ ነው ብለውታል።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሕማት፤ “ይህ አጋጣሚ በአገሪቱ ሰላም ለማስፈን ልዩ ዕድል ነው” ያሉ ሲሆን፤ ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች በቀጥታ ንግግር እንዲጀምሩ አሳስበዋል።

2014 ዓ.ም ከመጠናቀቁ በፊት በነበሩት ቀናት ከ30 በላይ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እንዲቆም ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

የአደራዳሪዎች ጉዳይ

የሰሜን ኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ የአፍሪካ ኅብረት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆን ልዩ የሰላም መልዕክተኛ አድርጎ ሾሞ፣ ሰላም ለማምጣት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

የውክልና ጊዜያቸው መጠናቀቁን ተከትሎ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ የአፍሪካ ኅብረት ኦባሳንጆ የተሰጣቸውን የኃላፊነት ጊዜያቸው እንዲራዘም ማድረጉን አስታውቋል።

“በእሳቸው ላይ ያለኝ ሙሉ እምነት ደግሜ በማረጋገጥ፣ ከሁለቱም ወገኖችና ከዓለም አቀፍ ተወካዮች ጋር ያለውን ግንኙነት በመቀጠል በኢትዮጵያና በቀጠናው ሰላምና እርቅ እንዲመጣ አበረታታለሁ” ሲሉ የኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሕማት በትዊተር ገፃቸው ፅፈዋል።

ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ በርካታ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ጥረት እና ግፊት ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወቃል።

የፌደራሉ መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች ወደ ጠረጴዛ ለመምጣት ቃል ገብተው ጊዜና ቦታ እንዲታወጅ ጥሪ እየቀረበ ባለበት ወቅት ነው አዲሱ ግጭት የተቀሰቀሰው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት ከህወሓት ጋር የሚደረግ ንግግር በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር መሆን አለበት የሚል የፀና አቋም ያለው ሲሆን፣ የትግራይ ኃይሎች ግን ልዩ መልዕክተኛው ኦባሳንጆ ለኢትዮጵያ መንግሥት “ቅርብ ናቸው” የሚል ተቃውሞ አላቸው።

በአሜሪካ የህወሓት ተወካይ የሆኑት አቶ ዮሐንስ አብርሃ፤ “ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የሚደረገው ድርድር በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት መሆኑ ቅር ባያሰኘንም፣ ኅብረቱ ተወካይ አድርጎ የሾማቸው ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ግን እንቀበላቸዋለን አላልንም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“አሁንም የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት የሰላም ድርድር ሂደቱን እንዲመሩት የእኛ ፍላጎት አይደለም” ብለዋል።

የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት ደብረፂዮን ገብረሚካኤል ባለፈው ሳምንት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በፃፉት ደብዳቤ፤ “ዳግም የተቀሰቀሰው ጦርነት ከዚህ በፊት ከነበሩት በላይ በትግራይ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ እልቂትን ይፈጥራል” ሲሉ አስጠንቅቀው ነበር።

ኡሁሩ ይመለሱ ይሆን?

ደብረፂዮን፤ “በተባበሩት መንግሥታት ጥረት ግጭቱ ከቆመ በኋላ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በባለሙያዎች የተደገፈ ዓለም አቀፍ አደራዳሪ ቡድን እንዲሰየም” ጠይቀው ነበር።

“በአፍሪካ ኅብረት ልዑካን ላይ ያለንን አቋም ከዚህ ቀደም ግልጽ አድርገናል” ያሉት ደብረፂዮን፤ በተባበሩት መንግሥታት የሚሾመው አደራዳሪ ቡድን አባላት “በእኛ ተቀባይነት ሊኖራቸው ይገባል” ሲሉ አሳስበው ነበር።

ነገር ግን ከጥቂት ቀናት በኋላ በአህጉራዊው ድርጅት አሸማጋይነት እንደሚስማሙ ቢገልጹም የፌዴራሉ መንግሥት ለዚህ የህወሓት “የሰላም ድርድር ጥሪ» እንዲሁም ለተባበሩት መንግሥታት ለቀረበው ጥያቄ እስካሁን ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል።

የትግራይ ኃይሎች የሰላም ድርድር በተሰናባቹ የኬንያ ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያ እንዲመራ ፍላጎት እንዳላቸው ሲገልጹ ቆይተዋል።

አዲሱ የኬንያ ፕሬዝደንት ዊልያም ሩቶ በኢትዮጵያ ሰላም ለማምታት በሚደረገው ጥረት ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የጀመሩትን ጥረት እንዲቀጥሉ መስማማታቸውን ተናግረዋል።

ነገር ግን፤ ኡሁሩ ኬንያታ በዚህ ሂደት ውስጥ ስለሚኖራቸው ሚና በይፋ የሚታወቅ ነገር የለም።

አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት፣ ኬንያ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ትልቅ ሚና አላት የሚል እምነት ያላቸው ሲሆን፤ በተለያዩ ጊዜያት የአሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት መልዕክተኞች በኢትዮጵያ ጉዳይ ከኬንያ መንግሥት ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።

የአሜሪካ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ የኢትዮጵያን እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድን ሰላም፣ ደኅንነትና መረጋጋትን አደጋ ላይ የጣለ ነው ትላለች።

በአገሪቷ “መጠነ ሰፊ ጥቃቶች፣ ጭፍጨፋዎች፣ ብሄር ተኮር ጥቃቶችን ጨምሮ ከባድ የመብት ጥሰቶችና መድፈር እንዲሁም ሌሎች ጾታዊ ጥቃቶች” መፈጸማቸውንና “የሰብዐዊ እርዳታ አቅርቦት” መስተጓጎል አጋጥሟል ሲል ዋይት ሐውስ ባለፈው ሳምንት ያወጣው መግለጫ ያትታል።

በዚህ ምክንያት ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የፈረሙበትና ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ጥሰቶች ፈፅመዋል በተባሉ የጦርነቱ ተሳታፊ አካላት ላይ ባለፈው ዓመት የተጣለው ማዕቀብ ባለበት እንዲቀጥል ወስነዋል።

ትዕዛዙ፤ ጦርነቱ እንዲራዘም አስተዋፅዖ ያደረጉ፣ የሰብዐዊ እርዳታ ተደራሽነት ያደናቀፉ፣ ተኩስ አቁም እንዳይደረግ እንቅፋት በመሆን በቀጥታ ተጠያቂ የሆኑ ወይም ተባባሪዎች ላይ ማዕቀብ እንዲጣል የሚፈቅድ ነው።

ማዕቀቡ የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናት እንዲሁም የአማራ ክልልና የህወሓት አመራሮች ላይ ያነጣጠረ ነው።

ወዴት ያመራ ይሆን?

ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ጦርነት በመጪው ጥቅምት 24 ሁለተኛ ዓመቱን ይደፍናል። በዚህ ሁለት ዓመት ውስጥ የአሁኑን ጨምሮ ሦስት ዙር ጦርነቶች ተካሂደዋል።

ሦስተኛው ዙር ጦርነት በለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ መልሶ ከማገርሸቱ በፊት ለአምስት ወራት ያህል ጋብ ብሎ የቆየ ሲሆን፣ በዚህ ወቅት የተለያዩ ወገኖች ተፋላሚዎቹን ለማሸማገል ጥረት ሲያደርጉ ቢቆዩም የተሳካላቸው አይመስሉም።

ባለፉት ሦስት ሳምንታት በተለያዩ አካባቢዎች ከባድ የሚባሉ ውጊያዎች እየተካሄዱ መሆናቸውና ከፍተኛ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች እንዳለ ይነገራል።

ከህወሓት በኩል በተለያዩ ስፍራዎች ጦርነቶች እየተካሄዱ ስለመሆናቸው እና በክልሉ ዋና ከተማ መቀለ ላይ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃቶች ከሚነገሩት መረጃዎች ውጪ፣ ከፌደራሉ መንግሥት በኩል አስካሁን የተባለ ነገር የለም። ቢቢሲ እና የተለያዩ የዜና ምንጮች ከመንግሥት በኩል ያሉ አስተያየቶችን ለማግኘት ቢጥሩም አልተሳካላቸውም።

መንግሥትም ሆነ የትግራይ አመራሮች ጦርነቱን በድርድር ለመቋጨት ፍላጎቱ እንዳለቸው ያሰውቁ እንጂ ያለፉት ጥቂት ሳምንታት ክስተቶች ግን ተፋላሚ ወገኖቹ ወደ ሰላም ጠረጴዛው የሚያደርሳቸውን እርምጃ እየወሰዱ ስለመሆናቸው አያመለክቱም።

 

 

Celebrity News
Daily Feta Posts

Recent post

Daily Feta

Other Post