ኢትዮጵያውያን ሴት አትሌቶች ደምቀው የታዩበት ምስጢር ምን ይሆን?

በኦሪገን የዓለም ሻምፒዮና ሜዳሊያ ያስገኙ ሴት አትሌቶች
እርግጥ ነው በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ቀድሞ ኢትዮጵያን የወከለው አትሌት ከበደ ባልቻ ነው።

ከበደ የፊንላንዷ ሄልሲንኪ በፈረንጆቹ 1983 ባዘጋጀችው ሻምፒዮና ለአገሩ እንዲሁም ለአፍሪካ የመጀመሪያውን ሜዳሊያ አመጣ።

ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ወደ ሜዳሊያ የተመለሰችው በኃይሌ ገብረ ሥላሴ አማካይነት ጀርመን ባዘጋጀችው የ1993 ዓለም ሻምፒዮና ነበር።

ነገር ግን በ1995 ላይ አዲስ ታሪክ ተፃፈ።

አትሌት ደራርቱ ቱሉ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የወከለች የመጀመሪያዋ ሴት አትሌት ሆና ወደ ስዊዲን አቀናች።

ደራርቱ በ10 ሺህ ሜትር ውድድር ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ ይዛ ተመለሰች።

ደራርቱ የከፈተችውን መንገድ ተከትለው ጌጤ ዋሚ ወርቅ፣ ቁጥሬ ዱለቻ እና አየለች ወርቁ በ1999 ስፔን ሲቪያ ላይ በተደረገው ውድድር የነሐስ ሜዳሊያ ይዘው ተመለሱ።

ወደ ካናዳ እናቅና። ኤድመንተን 8ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና አሰናዳች።

ደራርቱ ቱሉ ወርቅ፣ ብርሃኔ አደሬ ብር፣ ጌጤ ዋሚ እና አየለች ወርቁ ደግሞ ነሐስ ሰበሰቡ።

በአውሮፓውያን አቆጣጠር 2003 ዓ.ም. በፈረንሳይ ፓሪስ በተዘጋጀው ዘጠነኛው ሻምፒዮና፣ የ18 ዓመቷ ጥሩነሽ ዲባባ በ5 ሺህ ሜትር ታዋቂዎቹን ስፔናዊቷ ማርታ ዶሚንጌዝን፣ ብርሃኔ አደሬን እንዲሁም ኬንያዊቷ አዲት ማሳይን በአስደናቂ ብቃት በመቅደም ወርቅ አጠለቀች።

ኢትዮጵያ በዚህ ውድድር ከዓለም አራተኛ ሆና አጠናቀቀች።

2005 በፊንላንድ ሄልሲንኪ የተካሄደው ሻምፒዮና ግን ልዩ ነበር።

በ5 ሺህ እና በ10 ሺህ ውድድሮች ሴት አትሌቶች ከአንድ እስከ ሦስት ተከታትለው በመግባት “አረንጓዴው ጎርፍን” ለዓለም አስተዋወቁ።

ጥሩነሽ ዲባባ በሁለቱም ርቀቶች ወርቅ ደራርባ በማጥለቅ ኢትዮጵያ አሜሪካና ሩሲያን ተከትላ ከዓለም ሦስተኛ እንድትሆን አደረገች።

ሴት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ያስመገቡት ድል ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም።

ሶፊያ አሰፋ በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ሜዳሊያ ያመጣች አትሌት ናት።

ሴቶች አትሌቶቻችን በቻምፒዮናው መድረክ በ5 ሺህ እና በ10 ሺህ ሜትር ከአንድ እስከ ሦስት ተከታትለው በመግባት የሚደርሳቸው የለም።

ጥሩነሽ ዲባባ በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና 5 ጊዜ ወርቅ በማምጣት የአገሯን ሰንድቅ ዓላማ ከፍ ማድረግ ችላለች።

ዘንድሮ በአሜሪካዋ ኦሪገን ግዛት በተካሄደው ውድድርም ሴት አትሌቶች ደምቀው ታይተዋል።

ኢትዮጵያ ካገኘቻቸው አራት የወርቅ ሜዳሊያዎች ሦስቱ የተገኙት በሴት አትሌቶች ነው።

ለመሆኑ ሴት አትሌቶች በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ከጊዜ ጊዜ እየደመቁ የሄዱበት ምስጢር ምን ይሆን

አትሌት ጎተይቶም ገብረሥላሴ

የሜዳሊያ ሰንጠረዥ

“ፅናት”

“ዘንድሮ ያስመዘግበነው ውጤት ያስፈልገን ነበር” ትላለች የስፖርት ጋዜጠኛዋ ሃና ገብረሥላሴ።

“ሕዝቡ ለአትሌቶቹ ያደረገውን አቀባበል ስንመለከት፣ የተገኘው ውጤት ትርጉሙ ምን ያህል እንደሆነ የሚያሳይ ነው።”

ከአትሌቶች ምርጫና ከዝግጅት ጋር በተያያዘ እንደሌላው ጊዜ ባይሆንም የተወሰነ ስጋት እንደነበረ የምታወሳው ሃና፣ ሌሎች አገራት ካደረጉት ዝግጅት አንፃር ሲታይ ከተጠበቀው በላይ የሆነ ውጤት መጥቷል ትላለች።

ጋዜጠኛዋ አክላ ከዚህ በፊት ከነበሩት የቅርብ ጊዜ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ጋር ሲነፃፀር የዘንድሮው ውጤት ልዩ ነው የሚል ምልከታ አላት።

“ሄልሲንኪና ፓሪስ ጥሩ ውጤት ያመጣንባቸው መድረኮች ናቸው። ከቅርብ ጊዜ ትዝታችን ዴጉ ነው አነስ ያለ ውጤት ያመጣንበት። ከዚህ አንፃር የዘንድሮው ውጤት በልዩነት የሚታይ ነው።”

ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እስከ ዛሬ 33 የወርቅ ሜዳሊያዎችን ጨምሮ በጠቅላላው 95 ሜዳሊያዎችን መሰብሰብ ችላለች።

በዚህ ውጤት መሠረት ኢትዮጵያ ከዓለም ስድስተኛ፤ ከአፍሪካ ደግሞ ከኬንያ በመቀጠል ሁለተኛ ናት።

የዘንድውን የኦሪገን ውጤትን ጨምሮ ሴት አትሌቶች 47 ሜዳሊያ አስገኝተዋል። ወንድ አትሌቶች ደግሞ 48።

ሃና “የዚህ ምስጢሩ ፅናት ነው” ትላለች።

አትሌቲክስ ፅናት የጠይቃል የምትለው ሃና “ለሴቶች አዳላሽ እንዳልባል እንጂ፣ ሴት አትሌቶቻችን የሚያሳይት ዓይነት ወጥ አቋም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በወንዶች ላይ አታይም።

“አትሌቲክስ በጣም ተግቶ የመዘጋጀት፤ በተደጋጋሚ የሚመጡ የውድድሮችን ተጠቅሞ ብቃትን ማሳየት ይጠይቃል።”

ሃና፤ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ብቻ ሳይሆን ባለፉት ጥቂት የኦሊምፒክ ውድድሮች ሴት አትሌቶቻችን ደምቀው እንደታዩ ታወሳለች።

“በሁለቱም መድረኮች ሴት አትሌቶቻችን በብዛትም፣ በተፎካካሪነትም የበለጠውን ድርሻ ሲወስዱ እየተመለከትን ነው።”

ቢሆንም በትክክል ይሄ ነው ምክንያቱ ለማለት ጥናት ማድረግ እንደሚገባ ሃና ትናገራለች።

“ሴት አትሌቶች ምክር ይሰማሉ። ታዛዥ ናቸው። የሚሰጣቸውን ሥልጠና በትክክል ይተገብራሉ የሚባሉ ሐሳቦች ሲነገሩ እሰማለሁ” ስትል የስኬታቸውን ምስጢር ታስቀምጣለች።

አትሌት ለተሰንበት ግደይ ከኦሪገን መልስ በአዲስ አበባ

  የደራርቱ አመራር

የአገሯን ስም በተለያዩ መድረኮች ያስጠራችው ደራርቱ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሆና ከተመረጠች በኋላ ለውጥ ማምጣት ችላለች የሚል አስተያየት በተደጋጋሚ ይሰማል።

ነገር ግን ለደራርቱ ሁኔታዎች ሁሉ የተመቻቹ ነበሩ ማለት ከባድ ነው።

ደራርቱ ፌዴሬሽኑን መምራት ከጀመረች ወዲህ ሁለት ጊዜ በዓለም ሻምፒዮና፤ አንድ ጊዜ በኦሊምፒክ መድረክ፤ አንድ ጊዜ ደግሞ በዓለም የቤት ውስጥ ውድድር ተሳትፋለች።

በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ በተሰናደው የ2019 የዓለም ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ሁለት ወርቅ፣ አምስት ብርና አንድ ነሐስ ይዛ ተመልሳለች።

በዚህ ውድድር የኢትዮጵያ አትሌቶች በሚታወቁበት የመካከለኛና ረዥም ርቀት ውድድር የተለመደውን ወርቅ ማስመዝገብ ባይችሉም ተስፋ ያላቸው አትሌቶች ታይተዋል።

ኢትዮጵያ በመድረኩ በስምንት ሜዳሊያ አምስተኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች።

ከዚህ በኋላ በደራርቱ የተመራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ታላቅ ወደ ሚባለው የኦሊምፒክ መድረክ ነው ያቀናው።

በ2022 ቶኪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ ያገኘችው ሜዳሊያ ብዛት አራት ነበር።

ይህ ውጤት ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መድረክ ካመጣቻቸው ዝቅተኛ ከተባሉት የሚመደብ ነው።

ቀጥሎ ኢትዮጵያ የተሳተፈችበት ዓለም አቀፍ መድረክ ባለፈው መጋቢት የተካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ፍልሚያ ነው።

ይህ መድረክ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ደምቀው የታዩበት ነበር።

ኢትዮጵያ፤ በአራት ወርቅ፣ በሦስት ብርና በሁለት የነሐስ አሜሪካንን አስከትላ ከዓለም ቁንጮ ሆና አጠናቃለች።

በደራርቱ አመራር ወደ ኦሪገን የተጓዘው የአትሌቲክስ ቡድን አራት ወርቅ፣ አራት ብርና ሁለት ነሐስ በመሰብሰብ ከዓለም ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል።

ሃና፤ ደራርቱ ቱሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየመጣ ላለው ውጤት ብቸኛዋ ምክንያት ባትሆንም ትልቅ ሥፍራ እንዳላት ትናገራለች።

“በውድድር ዝግጅት ወቅት እየመጣች የምታበረታታ ናት። ከልጅነትህ ጀምሮ የምታደንቃትን ሴት በቅርበት ማግኘት በራሱ ትልቅ ሚና አለው። እንደሷ ጀግና የመሆን ፍላጎት እንዲያድር፤ እንደሷ ከተወዳዳሪነት አልፎ ወደፊት ለሌሎች ምሳሌ የመሆን ምኞት እንዲያድር ያደርጋል።

“እንኳን ለአትሌቶች ቀርቶ ለእኛ ራሱ፤ ደራርቱን ማግኘት የሚሰጠው መነቃቃት የተለየ ነው።”

ጎተይቶም ገብረሥላሴ

ተጨማሪ ጫናን መቋቋም

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደሚታየው የዘንድሮውም የአትሌቲክስ ሻምፒዮና አገር ውስጥ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ የተንፀባረቀበት ነው።

ጉዳፍ ፀጋይ የ5 ሺህ ሜትር ውድድርን ባሸነፈችበት ወቅት አንድ ተመልካች የትግራይ ክልል ባንዲራን ይዞ ወደ መሮጫ ትራክ ሲገባ በቀጥታ ቴሌቪዥን ሥርጭት ታይቷል።

ከዚህ በፊትም አትሌቶች ፖለቲካዊ መልዕክት ያዘለ ምልክት በሩጫ መደረኮች ላይ ማሳየታቸው የሚዘነጋ አይደለም።

ከአራት የወርቅ ሜዳሊያዎች ሦስቱን ያስገኙት ሴት አትሌቶች ከትግራይ ክልል የመጡ ናቸው።

አሁን ባለው የእርስ በርስ ግጭት ምክንያት አትሌቶቹ ከቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘት አለመቻላቸውም ይታወቃል።

አትሌቶቹ ይህን ጫና ተቋቁመው ድል መንሳታቸው የሚደነቅ ነው ሲሉ በርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ሃናም ይህ የሚደነቅ ነው ትላለች።

“ባለው ፖለቲካ ምክንያት በቤተሰብ፣ በበማኅረሰብ ያለው ጫና፤ በተለይ መጀመሪያ አካባቢ ከአትሌቶች ጋር የጋራ ልምምድ ማድረግ እስኪከብድ ድረስ መድረሱ፤ በተመሳሳይ መጀመሪያ አካባቢ የውድድር ዕድል አለማግኘትን የመሳሰሉ ጫናዎች ተቋቁመው ነው ውጤት ያመጡት።”

ሃና አትሌቶች የተሸከሙት ጫና ከምናነገርውም፤ ከምናስበውም በላይ ነው ትላለች።

“ጫናው የበለጠ ጠንካራ እንዲሆኑ፤ ለፅናት እንዲቆሙ አድርጓቸዋል ብዬ አስባለሁ። ለዚያም ነው ሦስቱም አትሌቶች ላይ ስሜታዊነት የተመለክተነው። ውድድሩን እንዳገባደዱ የሚታይባቸው ስሜት ደስታና ሃዘን የተደበላለቀበት እንደሆነ ይታያል። ከቤተሰቦቻቸው የተሰሙትን አስተያየቶች ስትመለከት ደስታህን ጎዶሎ ሊያደርገው እንደሚችል እውን ነው።”

አትሌቶቹ አገር ቤት ሲገቡ ሞቅ ያለ አቀባበል ጠብቋቸዋል።

ሐሙስ ዕለት በቤተ-መንግሥት በተካሄደው የዕውቅና እና ሽልማት መርሃ ግብር ላይ የተገኙት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተለይ ደግሞ ሴት አትሌቶች ያመጡትን ውጤት በማድነቅ ምስጋናቸውን ገልጠዋል።

ፕሬዝዳንቷ “ለተጨነቀው፣ ላዘነው፣ ለተከዘው፣ ኑሮ ለከበደው፣ እንደ አገር የት ነን ለሚለው ፈገግታን ያስገኘ ነው። . . . እኔ ላሸነፍ፣ እኔ ልቀደም ብቻ ሳይሆን በመተባበር በቡድን በመስራት ለሌሎች በር የከፈቱ አይተናል፤ ለተሰንበት የሰጠሽን ትልቅ ትምህርት ነው” ብለዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን አትሌት ደራርቱ ቱሉ በበኩሏ በትግራይ ያለው ሁኔታ ከክልሉ የመጡ አትሌቶች ቤተሰቦቻቸው ማግኘት አስቸጋሪ እንዳደረገው ተናግራለች።

“በትግራይ አትሌቶች አሉን፤ አልመጡም። ስለዚህ ባሉበት ልምምድ እንዲጀምሩ፤ አስፈላጊ አትሌቶች ደግሞ እዚህ እንዲመጡ መንግሥትም ለእነዚህ አትሌቶች መንገድ ከፍቶ ቤተሰቦቻቸው እንዲያገኙ ትብብር እንዲያደርግልን እጠይቃለሁ” ብላለች።

ኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሴቶች ማራቶን ድል የቀናት በማሬ ዲባባ አማካይነት በ2015 የቤይጂንግ ውድድር ላይ ነበር።

በዘንድሮው ሻምፒዮና የርቀቱን ክብረ ወሰንን በመስበር ወርቅ ያጠለቀችው አትሌት ጎተይቶም ገብረሥላሴ ከውድድሩ በኋላ በተደበላለቀ ስሜት ውስጥ ሆና ታይታ ነበር።

“የቤሰተብ ናፍቆት እንጂ ሌላ የደረሰብኝ ጫና የለም። ምግብ ስበላ ቤተሰቦቼ ትዝ ይሉኛል። ይሄ ተፅዕኖ ይፈጥራል። ሰው ሲደሰት አይቻለሁ። ቤተሰቦቻችን ያሉበት ቦታ ብንሄድ ደግሞ የእኛም ደስታ ሙሉ ይሆን ነበር። የእግር እንጂ የአዕምሮ እረፍት አልነበረንም” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

ጎተይቶም ከመንግሥት ዕውቅና እና ሽልማት ከተበረከተላት በኋላ ለቢቢሲ በሰጠችው አስተያየት፤ “ሁሉም አሸንፋለሁ ብሎ እንደሚገባው እኔም አሸንፋለሁ በሚል ተስፋ ነው የገባሁት” ብላለች።

“ከተፎካካሪዬ ጋር ስንሄድበት የነበረው ፍጥነት የአስር ሺህ እንጂ የማራቶን አይመስልም ነበር፤ ይህም ውድድሩን ፈታኝ አድርጎታል።”

“ከውጤት አንፃር አብዛኛው በሴቶች የመጣ መሆኑን ሳይ ደስተኛ አድርጎኛል፤ ግን ወንዶቹም ጠንክረው ሠርተዋል። ማራቶን ላይ ወንዶች ማሸነፋቸው ደግሞ እኛም እንድናሸንፍ ሞራል ሆኖናል።”

Celebrity News
Daily Feta Posts

Recent post

Daily Feta

Other Post