ኤኤች-64 አፓቺ /AH-64 Apache/ ወታደራዊ ሄሊኮፕተር

አሜሪካኖቹ ከሚመኩባቸው ተዋጊ ሄሊኮፕተሮች መካከል አንዱና ዝነኛው ነው፡፡ ኤኤች-64 አፓቺ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰራው ማክዶኔል ዳግላስ በተባለ ኩባንያ ነበር፡፡ በርግጥ ይህ ኩባንያ የኋላ የኋላ እ.አ.አ በ1997 በቦይንግ ኩባንያ መጠቅለሉን ልብ ይሏል፡፡

እ.አ.አ በ1984 በአሜሪካ አየር ሀይል ውስጥ መሳተፍ ከጀመረ በኋላ ግብጽ፣ ግሪክ፣ ህንድ፣ እስራኤል፣ ሲንጋፖር፣ ኔዘርላድ፣ ጃፓን፣ ሳውዲአረቢያ፣ ኳታር፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ዩናይትድ ኪንግደም የሄሊኮፕተሮች ፈላጊ ሆነዋል፡፡

ቦይንግ እስከአሁን ድረስ 2200 የሚሆኑ እነዚህን ገዳይ ወታደራዊ ሄሊኮፕተሮች ለአሜሪካ ጦር እና ለሌሎች ታጣቂ ሀይሎች አምርቶ ያስረከበ ሲሆን፡፡ 1200 የሚሆኑት ደግሞ በአሁኑ ሰዓት በአለምአቀፍ ሀይሎችና በአሜሪካ አየር ሀይል ውስጥ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

ታዲያ ለመጀመሪያ ጊዜ አገልግሎት ላይ የዋለው በአሜሪካ ጦር አማካኝነት ፓናማ ውስጥ ሲሆን ኢራቅን ከኩዌት ለማስወጣት በተደረገው የበርሃው ማዕበል ተልዕኮ ላይም ብቃቱን ያስመሰከረው ይህ ሄሊኮፕተር በአለም ላይ ያልተሳተፈባቸው ተልዕኮዎች ጥቂት ናቸው ይባላል፡፡

 

 

በርግጥ አፓቺን አስፈሪ ያደረገው ነገር ምንድን ነው?

ባለ 30ሚሜ አውቶማቲክ ቦይንግ ኤም230 የሚባል መሳሪያ ታጥቋል፡፡ በሚገርም ሁኔታ መሳሪያው በደቂቃ ውስጥ 625 ጥይቶችን በመትፋት ጠላትን ፋታ በማሳጣት አይቀጡ ቅጣት ይቀጣል፡፡ ምናልባት ደግሞ ለጥይቱ አልበገርም የሚል ባላጋራ ከተገኘ ምንም ችግር የለም፣ አፓቺ ከ8ኪ.ሜ እስከ 12 ኪ.ሜ ድረስ ከሰማይ ወደ ምድር እየተምዘገዘጉ ሄደው ማደባየት የሚችሉ ሎንግቦው ሄልፋየር የሚባሉ ሚሳኤሎችን ታጥቋል፡፡

ምን ይሄ ብቻ በአየር ላይ ውጊያ ሊፋለመው የሚደፍር ካለ አፓቺ ለአየር ላይ ፍልሚያ በማሰብ ከታጠቃቸው ስቲንገር፣ ኤአይኤም-9 ሳይድዊንገር፣ ሚስትራል እና ሳይድአርም በተባሉ ሚሳኤሎች የሚሰጠውን አፀፋ ቆም ብሎ ማሰብ አለበት፡፡ ትርፍና ኪሳራ ሳይሰራ ይህን ገዳይ ሄሊኮፕተር መተንኮስ ዋጋ ያስከፍላል፡፡

በአጠቃላይ ባሁለት ሞተሩ አፓቺ የወታደራዊ ሄሊኮፕተር ኢንዱስትሪን ወደቀጣዩ ደረጃ ያመጣ ቴክኖሎጂ ነው ተብሎ ተመስክሮለታል፡፡ አሁን አሁን ተሻሽለው የመጣው የዚህ ሄሊኮፕተር ዝርያዎች ደግሞ እጅግ የረቀቁ ናቸው፡፡ ፓይለቱ የሚያጠልቀው ሄልሜት ውስጡ በእስክሪን የተለበጠ ነው፡፡ ፓይለቱ ማንኛውንም መረጃ እዛው አይኑ ላይ አየተመለከተ የውጊያ ስልቱን እየቀያየረ መፋለም ይችላል፡፡ እንደው ይግረማችሁ ሲሉ በደቂቃ 625 ጥይቶች የሚተፋው መሳሪያ ከዚህ ሄልሜት ጋር የተገናኘ ሲሆን የፓይለቱን የአይን እንቅስቃሴ እየተከተለ ጠላቶቹን አፈር ከድሜ ማብላት ሁሉ ይቻለዋል፡፡

ሌላው የዚህ ሄሊኮፕተር አስገራሚ ብቃቱ ደግሞ ጠላቶቹን ቀድሞ በማየት ፓይለቱ የአፀፋ እርምጃ እንዲወስድ ማስጠንቀቁ ነው፡፡ ለዚህም ሲባል በተገጠመለት የኢንፍራሬድ እና ሌሎች አነፍናፊዎች አማካኝነት በ31 ማይል ርቀት ውስጥ የሚገኙ 256 ኢላማዎችን የመከታተል ብቃትን ተላብሷል፡፡

ውድ የሰዋስው ቤተሰቦች ኤኤች-64 አፓቺ /AH-64 Apache/ ገዳይ ወታደራዊ ሄሊኮፕተር!

Celebrity News
Daily Feta Posts

Recent post

Daily Feta

Other Post