ከዕለታት ግማሽ ቀን ምዕራፍ አንድ – ክፍል አንድ

የዛሬ አሥራ ሦስት ዓመት እግዚእብሔርን ለመሆን ተመኝቼ ነበር፤ አልተሳካልኝም፡፡ .
እግዚእብሐርን መሆን ስላልተሳካልኝ “በቃ ለምን ሰይጣን አልሆንም?” የሚል ሐሳብ
ውል ብሎብኝ፡ ሰይጣን ለመሆን ሞከርኩ እሱም ቢሆን እንዲህ እንደሚወራው ቀላል አልነበረም(ክፋት በሰይጣን እጅ ያምር፤ሲይዙት ያደናግር) እንግዲህ ሁለቱንም ካልሆንኩ ራሴን ልሁነውና የመጣውን ልጋፈጠው” ብዬ እግዜርነትንና ሰይጣንነት ልለካ አውልቄ ያስቀመጥኩትን እኔነት ፍለጋ ዙሪያዬን ባስስ ራሴም የለሁም፡፡ ይሄ ደግሞ ማነው?” እስክል ራሴን ፈጽሞ የማላውቀው አዲስ ፍጡር ሆኖ አገኘሁት፡፡ይኼው እስራ ሦስት ዓመት ጊዜ ፈጣን ነው፡፡ እንደ ደራሽ ጎርፍ ጠራርጎ የማይወሰድብን እያግበሰበሰም አምጥቶ የማይጭንብን ጉድ የለም፡፡ የአሥራ ሁለተኛ ክፍል የማትሪክ ውጤት የተነገረበት ሰሞን ነበር፤ ከብዙዎች ተመርጠን ወደ ዩኒቨርስቲ መግቢያ ከፍተኛ ውጤት ስላመጣን “በምድር ላይ መከፈት የማንችለው በር የለም! የሚል የወጣትነት የዋህ ትዕቢት፣ ወጣት ልባችንን የሞላበት ጊዜ፣ የሰፈሩ ወጣት ሴቶች እናተ ልጆች ያሻችሁን ጠይቁን” በሚል ዘወርዋራ ፈገግታ፡ የዕድሜ እኩያ እንዳልገንን ሁሉ ለትልቅ ሰው ከሚሰጥ አክብሮት ጋር ይሽኮረመሙልን የነረበት ጊዜ( ለእናተ ያልሆነ ሴትነት ዓይነት) ትምህርት ላይ ደከም ያሉ የሰፈራችን ልጆች በወላጆቻቸው እንደነሱ አትሆኑም?” እየተባሉ ስማችን ከኩርኩም ዝናብ በፊት እንደመብረቅ ጆሯቸው ላይ ይንባረቅባቸው የነበረበት ጊዜ “ምነው እነዚህን ልጆት ከዚህ ሰፈር በነቀለልን”ብለው በሆዳቸው ሳይረግሙን አልቀሩም (መማር ባይሆንላቸው  መራገም አያቅታቸው) አላፊ አግዳሚው በኩራት ፈገገ ይልልን በነበረበት ጊዜ ይኼም  ፈገግታ ትምህርት ሚንስቴር እውቅና ሰጥቶቷቸው ከፈተነን “ኬሚስትሪና ማተማቲክስ ምናምን ‘ሰብጀክቶች በላይ፡ የሰፈሩ ሰው በአደራ ሰጥቶን በከፍተኛ ውጤት ላለፍነው “በጎ አርአያነት ነፍሳችን ካርድ ላይ የሚያስቀምጠው “A” በነበረ ጊዜ ያ ጊዜ ሕይወት ያለ የሌለ እንደ በረዶ የነጣ ጥርሷን ፈገግ ብላ ታሳየን የነበረችበት የክረምት ወር ነበር፡፡ ለእኔና ለጓደኛዩ መሐሪ! “ምን ጓደኛ ናቸው እነዚህ፣ ወንድማማች እንጂ እማምላክንም ይሉ ነበር የሚያውቁን ሁሉ፡፡ አልተጋነነም፡፡

አንድ ሰፈር ነው ተወልደን ያደግነው፡፡ በቤታችንና በቤታቸው መሃል ያሉት አንድ አምስት ቤቶችና፣የሰፈሩ ልጆች ኳስ የምንጫወትበት አቧራማ ሜዳ ብቻ ነበሩ የመሃሪ እናት ዝንጥ ያለች የቢሮ ሠራተኛ ነበረች፡ ማሚ የምንላት መልከመልካም እናት፤ አገር ምድሩ እትዬ ሮሚ” የሚላት፡ ዘርፋፋ ባለ ከሸከሽ ቀሚስ በመቀነት ሸብ አድርገው ነጠላ በሚያጣፉ እናቶች መሃል ጉልበቷ ድረስ ያጠረ ቀሚስ የምትለብስ፣ ቀጥ ያለ አቋም ያላትና ጸጉሯን ባጭሩ የምትቆረጥ በእውቅ የተቀረጹ ዓምዶች በመሳሰሉ ውብ ጠይም እግሮቿ በተራመደች ቁጥር፣ እንደ ሙዚቃ በተመጠነ ርቀት ቋ ቋ ቋ የሚል ድምፅ በሚያወጣ ባለረዥም ተረከዝ ጫማ የምትውረገረግ ዘመናዊ እናት፡፡ ባሏ የጸሐፊነት ሥራዋን እንድታቆም አድርጓት በኋላ ተወችው እንጂ፡ በፊት በፊት መሐሪን ጧት እቤታችን አምጥታ ለእናቴ ትተወውና ወደ ሥራዋ ትሄዳለች፤ ስትመለስ  ትወስደዋለች።አብረን ነው ያደግነው፡፡ ነገሩ ዋጋ ተቆርጦለት የልጅ ጠባቂነት አይሁን እንጂ፡ ለቤተሰቦቼ በሰበብ አስባቡ ገንዘብም ቁሳቁስም መደገፏ አይቀርም ነበር፡፡ ከዚያ ዕድሜያችን ጀምሮ እኔም ሆንኩ መሐሪ ሌሎች የመንደሩ ልጆች ጋር ቅርበታችን እምብዛም ነበር፡፡

ማሚ ሁለታችንንም ግራና ቀኝ ይዛን ቄስ ትምህርት ቤት ስትወስደን ትዝ ይለኛል፡፡ በሕፃንነት ዕድሜያችን (አምስት ዓመት ቢሆነን ነው) ያኔ መንገድ ላይ ሰላም ያሏትን ሰዎች ስም ዝርዝር ብባል፣ አንድ ባንድ አስታውሳቸዋለሁ፤ በተለይ ወንዶቹ የሚያሽቆጠቁጣቸው ነገር ነበር! ታዲያ መምሬ ምስሉ ለተባሉ ፊደል አስቆጣሪ ስታስረክበን፣ በሹክሹክታ እንዲህ ስትላቸው ሰማኋት”የኔታ አንድ ላይ ከተቀመጡ መላም የለው፧ አነጣጥለው ያስተምሯቸው መሐሪ ግን እንዲህ ስትል አልሰማኋትም አለኝ፡ አቋቋማችን እኮ ከእኔ ይልቅ እሱ ይቀርብ ነበር፡፡ ስንት ዓመት አልፎ፣ ካደግን በኋላ፣ ማሚን ስንጠይቃት “ውይ! በምን አስታወስከው ልጄ?” ብላ በሳቅ ፍርስ አለችና ብያቸዋለሁ እውነትህን ነው ብላ አመነች። መሐሪ እየሳቀ የሆነ ሼባ ነገር ነው ነገር አይረሳም አለ ሁልጊዜም ዝንጉቱን የሚያስተባብለው፤ እኔን ነገር ከነከስኩ የማለቅ ሽማግሌ በማድርግ ነበር፡፡ ጎን ለጎን ተቀምጠን ሰዎቸ ለሁለታችንም ያወሩልንን አለፍ ስንል “ምናሉ? ብሎ የሚጠይቅበኝ ጊዜ ብዙ ነው ለዙሪያው ቸልተኛ ነበር!

መምሬ ምስሉ የማሚን አደራ ለመጠበቅ በቁጣም በአለንጋም ሊነጣጥሉን ብለው ብለውን አልሆን ስላላቸው እኒህ ልጆች፣ እንደ ዳዊትና የዮናታንን ጓደኝነት ነብሳቸው አብሮ የተሰፋ ነው!” ከሚል ምሳሌ ጋር እንደ ፍጥርጥራችሁ ብለው ተውን፡፡ ለረዥም ጊዜ ዳዊትና ዮናታን ረባሽ የቄስ ትምህርት ቤት ሕፃናት ይመስሉኝ ነበር፣ ሮሐ ናት በኋላ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ ጓደኛሞች መሆናቸውን የነገረችን (ሰንበት ትምህርት
ቤት ተማርኩ ብላ) ይኼንንም የነገረችን ቀን አብረን ሰምተን ዞር ስትል መሐሪ ምናለች” ብሎኛል፣ አድጎም አልለቀቀው! ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አስራ ሁለተኛ ክፍል እስክንደርስ እኔና መሐሪ ተነጣጥለን አናውቅም።አንድ ክፍል፣ አንድ ወንበር፣ አልፎ አልፎ ጎን ለጎን ያሉ ክፍሎች፡ ግን አንድ ትምህርት ቤት ነበር ያሳለፍነው።

ዐሥረኛ ክፍል ስንደርስና መሐሪ ሮሐ ከምትባል ልጅ ፍቅር ሲጀማምረው ነበር፣ ሦስተኛ ሰው አብሮን የታየው፤ያኔ ታዲያ ሮሐን ወደድኩ ሲል (ባይወዳት ነበር የሚገርመኝ ሁለታችንም ብርክ ያዘን፤ ነገሩ ጋሼ ጋር ከደረሰ ሁለታችንንም ከገጸ-ምድር ያጠፋናል የሚል ፍርሃት ነበር ያራደን፡፡ ጋሼ የምንለው የመሐሪን አባት ነው፡፡ ጋሽ ዝናቡ ዶፍ ቢሉት ይሻል ነበርኮ” እንባባላለን እኔና መሐሪ ስናማው። ጋሽ ዝናቡ ሲቆጣ፣ ቁጣው ልክ እንደ ርዕደ መሬት ከሰው አልፎ የቤቱን እቃዎችና የግቢውን ዛፎች የሚያንዘፈዝፍ ይመስል ነበር፡፡ ፊቱ የማይፈታ፣ ረዥም ቦክሰኛ የሚመስል ሰው ነበር፡፡ ዳኛ ስለሆነ ነው መስል ቤታቸው ፍርድ ቤት ነበር የሚመስለኝ፡፡ መሐሪም፣ ማሚም ተሽቆጥቁጠው ነው የሚኖሩት፡፡ ደግነቱ ቁጣው በየአራት ዓመት አንዴ የሚከለት የተፈጥሮ አደጋ ዓይነት ነበር፡፡

ይቀጥላል…

Celebrity News
Daily Feta Posts

Recent post

Daily Feta

Other Post