የአለማችን አስደማሚው እና አስፈሪው ተልዕኮ Operation Opera

8 F-16 ተዋጊ አውሮፕላኖች፣ 6 F-15A ተዋጊ አውሮፕላኖች፣ ሁለት እጅግ በጣም ከባድ የሆኑ ከወደቁ በኋላ ዘግየት ብለው የሚፈነዱ ቦምቦች፣ 14 ተዋጊ አውሮፕላኖችን ራዳር 1 የንግድ አውሮፕላን አድርጎ እንዲያነባቸው የሚያደርግ አጅግ አስገራሚ የአሰላለፍ ብቃት፣ ተመሳሳይ ፓይለት የተለያዩ አገራት ድመፀትና ቋንቋ፣ አንድ በጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ ያለ አገር፣ ደግሞም ሌላ አይኗን ለአፍታ የማታረግብ አገር … ብዙ ብዙ

ውድ የሰዋስው ቤተሰቦች ይህ አለማችን ካያቻቸው እጅግ አስደማሚ ተልዕኮዎች መካከል የሆነው ኦፕሬሽን ኦፔራ ነው፡፡

የኦፕሬሽኑ አጠቃላይ አንድምታ

ኦፕሬሽን ኦፔራ እ.አ.አ በ1981 የኢራቅን የኒውክሌር ኃይል ማመንጫን ያወደመ የእስራኤል የአየር ጥቃት ነበር። ኦሲራክ ኑክሌር ሪአክተር ተብሎ የሚጠራው ሬአክተር ከባግዳድ ደቡብ ምስራቅ ይገኝ ነበር። ሪአክተሩን የማጥፋት ተልዕኮው የተሳካ ሲሆን 10 የኢራቅ ወታደሮችን ጨምሮ 11 ሰዎች ተገድለዋል። ታዲያ የሪአክተሩ የቦምብ ፍንዳታ በሁለቱ ሀገራት መካከል በመካከለኛው ምስራቅ እስከ ዛሬ ድረስ ያለውን ውጥረት አጉልቶ የሚሳይ ምልክት እንደሆነ አለ፡፡

ነገርን ከስሩ

እ.አ.አ በ1976 ኢራቅ ለሰላማዊ ምርምር ጥቅም ላይ እንዲውል ከፈረንሣይ ሪአክተር ገዛች። የሪአክተሩ ግንባታ እ.አ.አ ከሶስት አመታት በኋላ በ1979 ተጀመረ። ፈረንሳዮች ኢራቃዊያን ለግንባታው ጥበቃ እንዲያደርጉለት ድጋፋቸውን ለገሱ፡፡

ነገር ግን የማታ የማታ እስራኤል ይህ ሪአክተር ለሰላማዊ አገልግሎት መዋሉ ላይ ከፍ ያለ ጥርጣሬ አለኝ ስትል ብቅ አለች፡፡ እንደውም አለች እስራኤል፣ እንደውም ኢራቃዊያን ከፈረንሳይ ያስመጡትን ሪአክተር የኑክሌር መሳሪያ ሊገነቡበት ይችላሉ፡፡ ስትል ጥርጣሬዋን አጠናከረች፡፡ እህሳ?

ነገሮች እንደሰደድ ተቀጣጠሉ፡፡ ከዚህ እስከዛ ድረስ ውጥረት ሆነ፡፡ በመጨረሻም እስራኤል ተቋሙ ለደህንነቴ ስጋት ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደረሰች፡፡ ለማውደምም ተነሳሳች፡፡

መረጃው፣ ትንታኔው፣ እቅዱ፣ ስልጠናው፣ ወታደራዊ ትንተናው፣ ሽርጉዱ፣ ለጦርነት የሚያስፈልገው ሁሉም ነገር ተሰናድቶ ካበቃ በኋላ እስራኤል በተመሳሳይ ሰዓት የክፍለ ዘመናችንን እጅግ አስደማሚም አደገኛም ተልዕኮ ለመፈፀም ተንደረደረች፡፡ አሁን ሁሉም ወደ ማምሻው እያዘቀዘቀ ይመስላል፡፡ ጥቁር ሰማይ ከኢራቅ ሪአክተር ግንባታ ላይ ሰፏል፡፡

ታሪክ ዘመኑን እ.አ.አ ሰኔ 7 1981 እንደሆነ ይነግረናል፡፡ 8 F-16 ተዋጊ አውሮፕላን አብራሪዎች እና 6 F-15A አብራሪዎች ለተልዕኮው ተመርጠዋል፡፡ F-16 አውሮፕላኖቹ ከወቀደቁ በኋላ ዘግየት ብለው የሚፈነዱ በርካታ ፈንጂዎችን ያጨቁ ሁለት ከበባድ ቦምቦች ታጥቀዋል፡፡ ተልዕኮው በይፋ ተጀምሯል፡፡

እዚህ ጋር ግን አንድ ፈተና መጣ፣ አውሮፕላኖቹ ሁለት የአየር ክልሎችን ሳይታዩ ማለፍ አለባቸው፡፡ የጆርዳናዊያንንና የኢራቃዊያንን የአየር ክልሎች፡፡ ነገር ግን 14 ተዋጊ አውሮፕላኖች ለዛውም በርካታ ፈንጂዎችን አጭቀው የያዙ ከበባድ ቦንቦችን የታጠቁ ሁለት አውሮፕላኖችን ከመካከላቸው አድርገው፡፡ የማይታሰብ ይመስላል፡፡

ምን ተሻለ?

ፓይለቶቹ አሰላለፋቸውን አስተካከሉ፡፡ አሰላለፋቸውም ለሚያቋርጧቸው አገራት ራዳሮች የሚያሳየው ምልክት አንድ የንግድ አውሮፕላንን ብቻ እንዲሆነ የሚያደርግ ነው፡፡ አሁን ደግሞ የአወሮፕላን ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ጉዳይ ይቀራል፡፡ ታዲያ ምን አደረጉ መሰላችሁ፣ አውሮፕላኖቹ ልክ ወደ ጆርዳናዊያን የአየር ክልል ሲገቡ ሁለት ፓይለቶች ብቻ በጆርዳናዊያን ቋንቋ እና ድምፀት የንግድ አውሮፕላን መሆናቸውን የበረራ ቁጥራቸውን ጨምሮ አስፈላጊውን መረጃ (የሀሰት) ተናግረው እንዲያልፉ ተፈቀደላቸው፡፡ ወደ ኢራቅ የአየር ክልል ሲገቡ ደግሞ አሁንም እኒሁ ፓይለቶች ጥርት ባለ አረብኛ ቋንቋና ድምፀት የንግድ አውሮፕላን መሆናቸውን አስመዝግበው አለፉ፡፡

ውድ የሰዋስው ቤተሰቦች 14ቱም ተዋጊ የጦር አውሮፕላኖች ወደ ጆርዳናዊያንም ሆነ ወደ ኢራቃዊያን የአየር ክልል ሲገቡ አሰላለፋቸው እጅግ በጣም ትክክል ከመሆኑ የተነሳ የአንድ አውሮፕላን አይነት ስለነበር የሁለቱም አገራት ራዳሮች ያገኙት ምልክት የአንድ አውሮፕላን ብቻ እንደነበር ልብ ይሏል፡፡ ለዛውም የንግድ አውሮፕላን፡፡

ተልዕኮው እንደቀጠለ ነው፤ አውሮፕላኖቹ አሰላለፋቸውን ሳይቀይሩ በደፈጣ ውስጥ ሆነው በኢራቃዊያን ሰማይ ስር እየበረሩ ይገኛሉ፡፡ ሰዓቱ ከምሽቱ 6፡35 ይላል፡፡ ኢራቅ ጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ ናት፡፡ እስራኤል ግን ኢላማዋን በቅርብ ርቀት እየተመለከተችው ነው፡፡

አውሮፕላኖቹ ሪአክተሩ ላይ እንደደረሱ ቦንቦቻቸውን አዘነቧቸው፡፡ ከጣሏቸው 16 ቦምቦች መካከል ግማሽ ያህሉ ኢላማቸውን በትክክል መቱ፡፡ ሁሉም ነገር በቅፅበት ከመኖር ወደ አለኖር ተሸጋገረ፡፡ ፍንዳታ እዚህም እዛም ሆነ፡፡ አውሮፕናሎቹ በፍጥነት አሰላለፋቸውን አፍርሰው የኢራቅን የአየር ክልል ሰንጥቀው ለመውጣት ተጣደፉ፡፡ የኢራቅ ኑክሌር ማብለያ ከባድ ፍንዳታ ከኋላ ይከተላቸዋል፡፡

ውድ የሰዋስው ቤተሰቦች ይህ አለማችን ካያቻቸው እጅግ አስደማሚ ተልዕኮዎች መካከል የሆነው ኦፕሬሽን ኦፔራ ነው፡፡

Celebrity News
Daily Feta Posts

Recent post

Daily Feta

Other Post