የዋጋ ንረት ተፅዕኖ እና መዳረሻው

ሰናይት አካሉ በ30ዎቹ እድሜ መካከል የምትገኝ ስትሆን የ3 ልጆች እናት ናት። ሰናይት የኮስሞቲክስ ንግድ ሥራዋን እየሠራች ሳለ ከአዲስ ማለዳ ጋር ተገናኝታለች። የኑሮ ወድነትን መቆጣጠር በአሁኑ ሰዓት ከባድ መሆኑን ታነሳለች። ‹‹ሚዲያዎች በተደጋጋሚ ሠርታችሁት ምንም ለውጥ ማምጣት ስላልተቻለ አለማውራት ይሻላል›› በማለት ነው የጀመረችው። ቤተሰብ በመመስረት 3 ልጆችን ያፈራችው ሰናይት በአሁኑ ሰዓት በንግድ ሥራ እየተዳደረች ትገኛለች። ልጆቿን ለማሳደግ ተቀጥራ ትሠራበት የነበረውን መሥሪያ ቤት በመልቀቅ የቤት እመቤት በመሆን ስትኖር መቆየቷን የገለጸችው ሰናይት፣ አሁን ግን ኑሮን ለማሸነፍ የግል ሥራ ጀምራ እየሠራች ነው። በርግጥ የንግድ ሥራዋ የተሳካ ነው ባይባልም ባለቤቷ የሚደጉመውን ቤተሰብ ለማገዝ የሚሆን ገቢ ታገኛለች።

‹‹አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እንኳን ሦስት ልጆች ተይዞ ራሳችን በልተን ማደር በጣም ከባድ የሆነበት ሁኔታ ላይ ደርሰናል›› ስትል ለአዲስ ማለዳ ገልጻለች። በተለይ ኹለት ልጆቿ ትምህርት ቤት የገቡ በመሆናቸው ከኑሮ መወደዱ ውጭ የትምህርት ቤት ክፍያ ራሱ ትልቅ ራስ ምታት መሆኑን ታነሳለች። ‹‹ልጆቼ መመገብ የሚገባቸውን ምግቦች ለመመገብ ከባድ ነው። አንዳንድ ጊዜ እንደውም የሚፈልጉትን ምግብ ሳንሰጣቸው ቤት ያፈራውን መመገብ ግዴታ ይሆናል›› ትላለች። ‹‹እንደ እኔ አይነት መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች የምንፈልገውን ያህል ባይሆንም በልተን እያደርን ነው። በእያንዳንዱ ምግብ ላይ የምናየው ጭማሪ ደሀውን ማኅበረሰብ ያገናዘበ አይደለም። እኔ ለንግድ ሥራዎቼ የምገዛቸው ዕቃዎች በሙሉ ውድ ናቸው። እንዴት በዚህ ዋጋ ደንበኛ ይገዛናል በማለት ሳልገዛ የምተዋቸው ምርቶች ቢኖሩም፣ አብዛኛዎቹ የምገዛቸው ዕቃዎች ከውጭ የሚመጡ በመሆናቸው ዶላር ስለጨመረ በማለት ምክንያት ይሰጡናል›› ስትል ትገልጻለች።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት አሁን ላይ በልቶ ለማደር ራሱ የማያስተማምንበት ደረጃ እያደረሰን እንገኛለን። ሚዲያዎች፣ መንግሥት፣ ነጋዴዎች፣ ሕብረተሰቡም ሆነ የኢኮኖሚ ምሁራን በተደጋጋሚ ሲወያዩበት የሰነበተ ጉዳይ የኑሮ ውድነት ነው። ለዚህ የኑሮ ውድነት ምሁራን እንደ ምክንያት ከሚያነሱት መካከል የዶላር መጨመር፣ የአገሪቱ አለመረጋጋት እና የምርት መጠን በበቂ ሁኔታ አለመኖርን ነው።

የምግብ ዋጋዎች መወደድን ከምርት መቀነስ ጋር አያይዘው የሚያነሱት ሚሊዮን በላይ፣ የአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነት ጥምረት አስተባባሪ ናቸው። በአገራችን ያለው 80 በመቶ የሚሆነው አርሶ አደር የሚያመርተው ምርት ላለው የሕብረተሰብ ክፍል ተመጣጣኝ አለመሆኑን ያነሳሉ። አርሶ አደሩ ትልቁን ድርሻ የያዘ ቢሆንም፣ ማምረት በሚገባው መጠን እያመረተ አለመሆኑን ሚሊዮን ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የኑሮ ውድነት ሰዎች የተመጣጠነ ምግብ መርጠው እንዳይመገቡ ያደረገ መሆኑንም አንሰተዋል። አንድ ሰው በቀን ውስጥ ማግኘት የሚገባውን የተመጣጠነ ምግብ ለመግዛት አቅም እንደሌለው አንስተው፣ ይህንን አቅም ግን ለመፍጠር ገቢውን ማሳደግ ተገቢ ነው ብለዋል። አገር ውስጥ እና ዓለም ላይ የሚገኙ ምግቦች ዋጋ መጨመርን ለመቆጣጠር የማምረት አቅም መጨመር አስፈላጊ መሆኑንም ሚሊዮን አንስተዋል።

‹‹ስለ ኑሮ ውድነት ስናነሳ በዋነኛነት ሊያስከትል የሚችላቸው ጉዳቶች በአራት ይከፈላሉ›› የሚሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማኅበራዊ ሳይንስ መምህር እንዲሁም የቢዝነስ፣ ኢኮኖሚ ልማትና ኢንተርፕረነርሺፕ አማካሪ የሆኑት ዜናው አለም ናቸው። እነዚህም ይላሉ ዜናው፣ በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በማኅበረሰብ እና በመንግሥት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች ናቸው። እነዚህ ተያያዠ የሆኑ አካላት በአንድ አገር ላይ የሚፈጠር የኑሮ ውድነት ጉዳት የሚያደርስባቸው ናቸው ሲሉ ዜናዊ ተናግረዋል።

በግለሰብ ደረጃ ኑሮ መወደድ የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ጫና ይፈጥራል ሲሉ ዜና ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል። ይህም የሥራ ማጣት ስለሚያስከትል ግለሰቦች ያለገቢ ሊቀመጡ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ ግለሰቦቹ ወደ ሌብነት ይገፋፋሉ። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ግለሰቡ ማግኘት ከሚገባው በታች ገቢ የሚያስገኝ የቅጥር ሥራ የሚሠራ ከሆነ ወደ ሙስና ለመግባት ገፊ ምክንያት ሊሆንም እንደሚችል ዜናዊ ገልጸዋል።

ሰዎች ኑሯቸውን ከማሸነፍ በተጨማሪ በልቶ ማደር ያሳስባቸዋል የሚሉት ዜናው፣ በልተው ለማደር ደግሞ በቂ ገንዘብ ማግኘት ይፈልጋሉ። ለዚህም ስርቆትን አማራጭ አድርገው መሔድ አንደኛው መንገድ ያደርጉታል። ስለ ስርቆት ከተነሳ አዲስ ማለዳ በተደጋጋሚ የታዘበችውን የስርቆት መንገዶች ለማንሳት እንሞክር። የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ የተደራጁ ግለሰቦች በተደጋጋሚ ዘረፋ ሲያካሂዱ ይታያሉ። ታክሲ ላይ ከተሳፈረ በኋላ ከረዳቱ፣ ከሹፌሩ እና ተባባሪ የሆነ ጓደኛ በማስቀመጥ ተሳፋሪን በማዋከብ ማስክ አድርጉ፣ ቀበቶ እሰሩ፣ ትርፍ ነህ እና ጎንበስ ብለህ እንለፋቸው እንዲሁም የተሳሳተ መስመር ነው የገባኸው በማለት ጥድፊያ የተሞላበት ንግግር የተዋከበው ተራው ነዋሪ ለተባባሪ ሌቦች እጅ ሲሰጥ ይስተዋላል። ኑሮን ለማሸነፍ ደፋ ቀና እያለ ያለን ማኅበረሰብ ለእንደነዚህ አይነት ሌብነት ሲዳረጉ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ ሌላ ፈተና ውስጥ ይከቱታል። እነዚህን ወደ ሌብነት ተግባር የሚገቡ አካላት ኑሮን ለማሸነፍ በሚደርግ ትግል ውስጥ የሚፈጠሩ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ የሥነ-ልቦና ቀውስ ውስጥ ይከታቸዋል ሲሉ ዜና ይገልጻሉ።

ወደ ሌብነት የሚገባው ወጣት ፈልጎት አይደለም። ሳይፈልግ ለገባበት ጸያፍ ተግባር ለመውጣት ሲያስብ ደግሞ የሚበላው የለውም። ስለዚህ በዚህ ኹለት አጣብቂኝ ውስጥ ራሱን ሲያገኝ ከፍተኛ የሥነ-ልቦና ቀውስ ውስጥ ይገባል። ፍርሀት፣ ስጋት እና የሥነ-ልቦና ጫናዎች ይፈጠራሉ። ይህ ደግሞ ሰዎች ተስፋ እንዲቆርጡ ያደርጋል። ይህ ተስፋ ማጣት ደግሞ ሰዎችን ራሳቸውን እስከማጥፋት ያደርሳቸዋል ብለዋል።

በማኅበረሰብ ደረጃ የሚፈጥረውን ቀውስ ምን እንደሆነ ያስረዱን ዜናዊ፣ ቤተሠብ የሚባሉት እናት፣ አባት፣ አያት እና ተጨማሪ አብረው የሚኖር አካላት ጭምር ሲሆኑ፣ የቤተሠቡ አስተዳዳሪዎች ቤተሠቡን ማስተዳደር የሚችሉበት አቅም ላይኖራቸው ይችላል። ትልቅ ቤተሠብ የሚያስተዳደር አንድ ቤት የሚጨነቀው በልቶ ስለማደር መሆኑ ምንም አያጠያይቅም።

ይህን የመኖር ዋስትና ለማረጋገጥ የቤተሠብ አስተዳዳሪው የሚያገኘው ገቢ ለሚያስተዳድረው ቤተሠብ በተመጣጣኝ ሁኔታ መዳረስ ይገባዋል። ነገር ግን እየታየ ያለው እውነታ ይህ አይደለም። የአብዛኛው ማኅበረሰብ ገቢ ከሚያወጣው ወጪ ጋር መጣጣም አልቻለም ሲሉ ዜና ያነሳሉ። ቤተሠብን ስናስብ በልቶ ለማደር በርካታ የገቢ ምንጮችን ለማግኘት እንደሚሯሯጡ ቢታወቅም፣ ይህ ሩጫቸው የሚፈልጉትን ያህል የገቢ ምንጭ ላያስገኝ ስለሚችል ቤተሠብ አባላት መካከል ግጭቶች ይፈጠራሉ። በባልና ሚስት መሀል መጨቃጨቅ፣ ልጆችን ላልሆነ የሥራ አይነቶች(እንደ ልመና )መማገድ ሊፈጠር ይችላል።

እነዚህ ችግሮች ደግሞ የቤተሠብ መበተን፣ ላልተፈለገ የሥራ ዘርፍ መሰማራት እና ለተለያዩ ወንጀሎች ሊገፋፉ ይችላሉ። ይህ ደግሞ ከማኅበረሰቡ ጋር ያለንን መስተጋብራዊ ቁርኝት ያሻክረዋል። በፊት የነበረን መረዳዳት እና ያለንን መካፈል የሚለው ኢትዮጵያዊ ባህላችን እየተሸረሸረ ይመጣል። የዕቁብ፣ ዕድር እና ሌሎች ከማኅበረሰቡ ጋር የሚያስተሳስሩነረ ክፍያ ያላቸው ኅብረቶች እየቀነሱ እንዲመጡ የሚያደርገው አንዱ የኑሮ ውድነት ነው። ይህ ደግሞ ያለንን ፍቅር በመቀነስ መገለል እንዲኖር ያደርጋል። መገለል ደግሞ የብቸኝነት ስሜት በመፍጠር የሥነ-ልቦና ቀውስ እንዲፈጠር ያደርጋል። ሰዎች ኑሮን ለማሻነፍ የሚጠቀሙት አማራጭ ብድር መሆኑ ይታወቃል። በዚህም መመለስ የማይችሉትን ብድር ይበደሩና መክፈል ሲያቅት ወዳልተፈለገ የኢኮኖሚ ጫና ይገባሉ። ይህ የብድር መጠን መጨመር ደግሞ ሰዎች ከሚያገኙት ላይ መቆጠብ እንዳይችሉ ያደርጋቸዋል።

በዚህ ወቅት በጣም ዝቅተኛ የነበረው የቁጠባ ባህላችን እየጠፋ እንዲሄድ ያደርገዋል ሲሉ ዜናው አንስተዋል። የኑሮ ውድነት እንደ አገር የሚፈጥረው ጫና ቀላል አለመሆኑን ዜና ያነሱት ሐሳብ ሲሆን፣ የሥራ አጥነት፣ ሥርዓት አልበኝነት መስፋት እና ሙስና መበራከት ይፈጥራል ብለዋል። ይህ የሥርዓት አልበኝነት መበራከት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና ይፈጥራል። ግለሰቦች ማድረግ ያለባቸው ገቢያቸውን መጨመር፣ ገቢና ወጪን ማመጣጠን፣ አላስፈላጊ ወጪን መቀነስ እንዲሁም ቅንጡ የሆኑ መገልገያዎችን መቀነስ ነው። ገቢን ለመጨመር ከሚረዱ ነገሮች አንዱ ተጨማሪ ሥራዎችን መሥራት አንዱና ትልቁ መፍትሔ ነው።

የውጭ ምንዛሬ በመደበኛ ወይንም በባንክ በኩል የሚደረገው ብዙ ጭማሪ ያሳየ ባይሆንም፣ በጥቁር ገበያ ያለው ምንዛሬ ግን በጣም በመጋነኑ ለኑሮ መወደድ ትልቅ ምክንያት ሆኗል የሚሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ አሶሼት ዲን፣ የቡና ባንክ ቦርድ ቼይርማን እና የኢንቨስትመንትና ፋይናንስ ረዳት ፕሮፌሰር ሰውአለ አባተ (ዶ/ር) ናቸው። ለዚህ የዶላር መጨመር ምክንያት በትግራይ አካባቢ የተፈጠረው ጦርነት እና የውጭ አገራት ያላቸውን ትብብር መቀነሳቸው መሆኑን ያነሳሉ። መንግሥት ጥቁር ገበያን በተመለከተ 13 የሚሆኑ ተቋማት ላይ የወሰደው እርምጃ የዶላርን መጨመር እንዳባባሰው ይገልጻሉ። በውጭ ምንዛሬ ዝውውር ምክንያት እርምጃ የተወሰደባቸው እነዚህ ተቋማት ዶላር እንዲጨመር ምክንያት ሆነዋል። ይህ የዶላር ጭማሪ የዋጋ ጭማሪን ያባብሰዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ በአብዛኛው የምንጠቀመው ከውጭ የሚገቡ ምርቶች እንደመሆኑ መጠን የዶላር መጨመር ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እንዲፈጠር ያደርጋል ብለዋል። የውጭ ጫናዎች መበርታት እና ጦርነት ደግሞ ኹለተኛውን ድርሻ በመውሰድ ኑሮ እንዲወደድ አድርገዋል። ጦርነት የተሸከመ ኢኮኖሚ ደግሞ ጫናዎች ይበረቱበታል። በቀጣይነት የሚጠቀሰው ምክንያት ነጋዴዎች የሚያደርጉት የምርት መደበቅ እና ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ ናቸው።

ነጋዴዎች ከውጭ በማይገቡ ዕቃዎች ላይም ዶላር ጨምሯል በማለት የሚያደርጉት ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና ይፈጥራል። በዚህ ጭማሪ በዋናነት ተጎጂ የሚሆነው ወርሐዊ ደሞዝተኛው እና የመንግሥት ሠራተኛው ነው ሲሉም አንስተዋል። ባንኮች የውጭ ምንዛሬን አስመጪዎች በሚፈልጉት መጠን ለመስጠት በቂ የሆነ ክምችት የላቸውም። ባንኮች ዶላር የሚያገኙት እየገዙ ነው። ኤክስፖርት ከሚያደርገው የንግድ ማኅበረሰብ፣ ውጭ የሚኖሩ ግለሰቦች ወደ ኢትዮጵያ ከሚልኩት፣ ቱሪስቶች አገር ውስጥ በሚገቡበት ወቅት ከሚመነዝሩት እና በእርዳታ ከሚገኝ ዶላር ነው ባንኮች ውስጥ የውጭ ምንዛሬ የሚገኘውና የሚንቀሳቀሰው። ባንኮች ጋር እና ጥቁር ገበያው ላይ የሚፈጠረው የምንዛሬ ልዩነት ከውጭ የሚልኩ ግለሰቦች ወደ ባንክ እንዳይመጡ፣ ቱሪስቶችም ባንክን እንዳይጠቀሙ ያደርጋል። በዚህ ጊዜ ባንኮች የሚያገኙት ዶላር መጠን በጣም ይቀንሳል። የዶላር መጠን ባንኮች ጋር የሚቀንስ ከሆነ መንግሥት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ከውጭ ለሚገቡ ምርቶች ዶላርን የመጠቀም ሁኔታ ይፈጠራል።

በዚህ ጊዜ ሌሎች ቅድሚያ ያልተሰጣቸው አስመጪዎች ወደ ጥቁር ገበያ ይሄዳሉ። ለዚህ መነሻ የሚሆነው ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉ አካላት በተፈጠረው የጥቁር ገበያ መጠቀም ሲሆን፣ ጉዳቱ ተመልሶ ወደራሳቸው የማኅረሰብ ክፍል ይሄዳል። ስለዚህ ከመንግሥት ቁጥጥር ባሻገር ሕብረተሰቡ ጥቁር ገበያውን ባለመጠቀም ባንኮች ጋር ዶላር እንዲጨምር ማድረግ ይገባዋል። ማኅበረሰቡ ጥቆማ በማድረግ ንቃተ ሕሊናውን በማሳደግ የግል ጥቅምን ከማስቀደም ይልቅ የአገር ኢኮኖሚን ለመጨመር ቢያስብ የዋጋ ንረት ይቀንሳል። አገራችን ውስጥ ያለው ማኅበረሰብ ቁጠባን ከሚያሳድግ ይልቅ ወጪን መሸፈን ብቻ ነው የሚያስበው። ይህ ደግሞ ገቢው ወጪውን ከመሸፈን ባለፈ ለቁጠባ የሚበቃ ባለመሆኑ ነው። ስለዚህ ሕብረተሰቡ ገቢውን ለማሳደግ ተጨማሪ ሥራዎች መሥራት አለበት። ሕገ-ወጥ የሆኑ ተቋማትን በማጋለጥ እና ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ ሲደረግ ግብይት ባለመፈጸም ሕገ-ወጥ አሠራሮችን መቀነስ ይቻላል ብለዋል።

Celebrity News
Daily Feta Posts

Recent post

Daily Feta

Other Post