ጎንደር ዩኒቨርሲቲ “የአንድ ተማሪ ለአንድ ቤተሰብ” ፕሮጀክቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ባለፉት ዓመታት ሲተገበር የቆየው “የአንድ ተማሪ ለአንድ ቤተሰብ” ፕሮጀክቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ።

አዳዲስ ተማሪዎቹን እየተቀበለ ጎን ለጎን መደበኛ የመማር ማስተማር ሂደቱን በተረጋጋ ሁኔታ እያከናወነ መሆኑን ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ወይዘሮ ይዳኙ ማንደፍሮ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በትምህርት ሚኒስቴር በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ዩኒቨርሲቲው አዲስ ገቢ ተማሪዎችን ከግንቦት አንድ ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ እየተቀበለ ይገኛል።

‹‹አንድ ተማሪ ለአንድ ቤተሰብ›› በሚል በዩኒቨርሲቲው ሲተገበር የቆየው መርሐ ግብር በዚህ ዓመትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያስታወቁት ወይዘሮ ይዳኙ፤ በአሁኑ ወቅት ለአዳዲስ ተማሪዎቹን የሚቀበሉ ቤተሰቦችን ለመለየት የቤተሰብ ምልመላ እየተካሄደ መሆኑንና በቀጣይነት ፕሮግራም ተዘጋጅቶ የተማሪና ቤተሰብ ትውውቅ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

በፕሮጀክቱ መሠረት ወደዩኒቨርሲቲው የተመደበ ተማሪን በጎንደር ከተማ ከሚገኝ ቤተሰብ ጋር በማስተሳሰር ልክ እንደልጃቸው አስፈላጊውን እንክብካቤና ቁጥጥር እንዲያደርጉለት ይደረጋል። ይህ አሠራር በተማሪዎች ውጤታማነት ላይ መልካም ለውጥ አሳይቷል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎች ምቹ፣ ሰላማዊና የተረጋጋ የምርምርና የመማሪያ አካባቢ ለመፍጠር የሚያደርገው እንቅስቃሴ አንዱ አካል መሆኑን ዳይሬክተሯ አስታውሰው፤ ተማሪዎች ተመርቀው ወደየአካባቢያቸው ሲመለሱም ከጎንደር ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዲኖራቸው ያደርጋል ሲሉ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ያለውን ወንድማማችነት በማጠናከር በኩልም የአንድ ተማሪ ለአንድ ቤተሰብ ፕሮጀክት ጉልህ ሚና እንዳለው ጨምረው ገልጸዋል።

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በዚህ ዓመት ከአምስት ሺ አምስት መቶ በላይ አዲስ ተማሪዎች ተመድበውለታል ያሉት ዳይሬክተሯ፤ ተማሪዎችን ለመቀበል ቀደም ብሎ ቅድመ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ጠቁመዋል።

አዳዲስ ተማሪዎቹን እየተቀበለ ጎን ለጎን መደበኛ የመማር ማስተማር ሂደቱን በተረጋጋ ሁኔታ እያከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።

በቅርቡ በከተማው ተፈጥሮ የነበረው ችግር ምንም ዓይነት ተጽዕኖ ሳያሳድርበት ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሂደቱ በተለመደው መልኩ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ገልጸዋል።

በቅርቡ በከተማው ከተከሰተው ወቅታዊ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የነበረው የፀጥታ መደፍረስ እንዲረግብ ከከተማው የፀጥታ አካላት ጋር የተቀናጀ ሥራ መከናወኑን አስታውሰው፤ ከተማውም ፍፁም ሰላማዊ የዩኒቨርሲቲውም ጸጥታ የተጠበቀ በመሆኑ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው ለመምጣት ምንም አይነት ስጋት የሚፈጥር ጉዳይ እንደሌለ አረጋግጠዋል።

ወላጆችም ልጆቻቸውን ያለምንም ስጋት በወቅቱ ወደ ዩኒቨርሲቲው በመላክ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማድረግ አለባቸው። በቀጣይነትም በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር ከከተማ አስተዳደሩና ከሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር ይሠራል ብለዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአንድ ተማሪ ለአንድ ቤተሰብ ቃልኪዳን ፕሮጀክት ከጎንደር ከተማ አስተዳደርና ከከተማው ማኅበረሰብ ጋር በመተባበር ተግባራዊ ሲደረግ የቆየ መቆየቱ የተገለጸ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ በጽሕፈት ቤት ደረጃ ተቋቁሞ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ፋንታነሽ ክንዴ

Celebrity News
Daily Feta Posts

Recent post

Daily Feta

Other Post