ጨረሬን የመጨረሻ ክፍል

“ያች ጨረር ብለው ጀመሩ “ያች ቀጭን ጨረር …ጌታ የተቀበረበት መቃብር ውስጥ እንደተከሰቱት መልእክት ለኔ የምስራች ነበርች… መቼስ ያየህ እንሆነ አባቴ ከፉ ነበሩ. የከፉ ከፉ ነጋ ጠባ እናታችንን መቀጥቀጥ ነው ፣መስከር ነው …የትም ከርመው መምጣት ነው እንዲሁ በየመጠጥ ቤቱ ሲጣሉ በሚወዱት የመጠጥ ቤት አምባጓሮ ሞቱ፡፡ በኋላ እናታችን እርሻም ከስቡም ብቻዋን አልሆን ሲላት፣ አንዱን ከወደ ቆላ
የመጣ ባለጌ ሰው ነው ብላ አገባች፡፡ መቼስ ለመከራ ሲፈጥር አይለቅህ … የባሰ ነውረኛ ሁኖ ቁጭ አለ፡፡ ገና አንድ ፍሬ ልጅ ነኝ፣ እንጃ ይችን የዘውዲቱን ልጅ ባክል ነው (የጎረቤታችን ዘውዲቱ ልጅ ገና ዘጠኝ አመቷ ነው) ሰው ዞር ካለ ሳልፍም
ሳገድምም መጎንተል ነው ጭራሽ አንድ ቀን የላሞቹ በረት ስገባ ተከትሎ አነቀኝ የለበስኳትን ጥብቆዬን ሊያወልቅ ሲታገል ኡኡ…! ብዬ ስጮህበት እዛው እበቱ ላይ አንከባሎኝ ወጥቶ ሄደ፡፡ በገዛ ቤቴ ፈራሁ፤ የእናቴን ቀሚስ የሙጢኝ ብዬ በሄደችበት መከተል ሆነ፡፡ እሷ ሰው አግኝታ ሙታ ሂጅ አባትሽ ጋ ተጫዎች” ትለኛለች ..
በኋላ በሰበብ አስባቡ መግረፍ ሆነ ስራው ያመታቱ ያጨካከኑ ደሞ ተወው አታንሳው፡፡ የላሞቹ በረት የገባሁ እንደሆን ተከትሎ ከተፍ ነው፡፡ ወደ ጓሮ ለሽንት ዞር ያልኩ እንደሆነ እንደ ጥላ መከተል ነው፡፡ እንደው ነብሴ ተጨነቀች ፡፡ እናቴን አልነግር እንዲህ እንዳሁኑ ዘመን ልጅን ማን ይሰማል!? ገና ዘልዬ ሳልጠግብ ኑሮዬ ካሁን አሁን
መጣብኝ አነቀኝ ጭንቀት ሆነ፡፡ ገጠር ሽውታውም ኩፍኝም እያጣንም መቸም፣ አሞኝ
ጋደም ያልኩ እንደሆነ እናቴ ወጣ ካለች አትሂጅብኝ ለቅሶ ነው እየተንቀጠቀጥኩ
ተከትያት ደጅ ለደጅ ነው፡፡ ከመድኃኒያለምና ከሷ ሌላ ማን አለኝ? ታናናሽ እህቶቼና የሰፈሩ ውሪ ሁሉ ፈሪ ናት ከናቷ ቀሚስ ሥር አትወጣም” እያሉ መሳቂያ መዘበቻ አረጉኝ፡፡ ሲያመጣው ልክ የለው ይሄን ሆንኩ ሳትል እናታችን በሶስት ቀን በሽታ
ሞተችብን፡፡ ከሞቷም ካሟሟቷም በላይ ነብሴ መግቢያዋ መደበቂያዋ ጨነቃት እንዲህ እንዳይመስልህ የናቴ ልጅ ሐዘንተኛው እንኳን እግሩ ከቤት ሳይወጣ ቋንጣ እንዳየች ድመት ዓይኑ እኔ ላይ ነው፡፡

ሐዘኑም ምኑም ሲያበቃ ጎረቤት ቤት እየሄድኩ ብደበቅ አንጠልጥለው እያመጡ እቤቴ! እንዲቹ እንቅልፍ በዓይኔ ሳይዞር አድርና ቀን ወደእርሻው ሲሄድልኝ ቢመለሰ እንኳ ተኝቸ እንዳያገኘኝ እየፈራሁ… ከዚህ እንደጋሽ አለሙ ቤት የሚሆን ማሳው ውስጥ የተሰራ የእህል መክተቻ ጎተራ አለ… አርጅቶ እህል አይዝም እንዲሁ ቁሟል …ትልቅ ነው ያየህ እንደሆነ፣ ክዳኑን ገርበብ አርጌ እገባና መልሼ ከድኜ እዛው እተኛለሁ፡፡አሥር ጊዜ
እየመጣ ወንድሞቼን የት ሄደች? ሲል ይሰማኛል፣እንጃ ይሉታል፤ እየዛታ ይመለሳል፡፡
ድምጼን አጥፍቸ ዝም! ታዲያ በዛ ጨለማ የጭቃ ጎተራ ውስጥ ታፍኜ ለገመድ ማስገቢያ በተበሳው የጎተራው ሽንቁር በኩል የምትገባ ጨር ነበረች ከሰማይ ጀምሮ የተደበኩስት ጎተራ ድረስ ልትፈልገኝ የመጣች የእናቴ ነብስ ነው የምትመሰለኝ፡፡ ጨረሯ ፊቴ ላይ ስታረፍ እምባዬን የምታብስልኝ፡ የግዜር ጣት … በእጆቼ ስጫወትባት፣ እንደሰው በሹከሹክታ ሳወጋት እውላለሁ፡፡

ጠሃይ ስትጠልቅ ጨረሯ ስትጠፋ ያ ክፉ ሰውዬ አረቄውን ተግቶ እየደነፋ ይመጣል፡፡ ጨረሯ ማታ የምትጠፋው ያንን ከፉ ሸሽታ
ይመስለኝ ነበር፡፡ ማንም ሳያየኝ ከጎተራዬ እወጣና እየተንቀጠቀጥኩ ገብቸ እንዱ ጥግ
ኩርምት ብዬ ካሁን አሁን መጣብኝ እያልኩ እንዳፈጠጥኩ አነጋለሁ፤ነገም ያው! ቶሎ
ነግቶልኝ ለወንድምና እህቶቸ የሚቀምሱትን ቂጣም ሆነ እንፍሮ አሰናድቼ፤ እኔም ሸንብራ
ቢጤ ቆልቼ ቋጥርና ማንም ሳያየኝ ወደዛ አሮጌ ጎተራ ገብቼ ሸንብራዬን እየቆረጠምኩ
እዛች ጨረር ጋር ብሶቴን በልጅ ነብሴ እንሾካሾኩ እውላለሁ፡ ጨለማ ለኔ ጭንቀት ነው ጀንበር ዞር ካለች ንብሴ’ ትጨነቃለች እማማ ዝም ብለው ቆዩ ረዥም ዝምታ ታዲያ አንድ ሌሊት እዛቹ ጎጆ ጥግ ኵርምት እንዳልኩ …ኮቴ ሰማሁ በጨለማው ሊያቀኝ እያደባ ኑሯል፡፡ እንደው እንደፌንጣ ዘልዬ በጨለማው እንዴትም እንደከፈትኩት እንጃ በሩን በረገድኩና ልወጣ ስል ጥብቆዬን ቢያንቀኝ
ተተርትሮ እጁ ላይ ቀረ፣ ምናምኒት ሳልደርብ መለመላዬን በደረቀ ሌሊት ኡኡታዬን እያቀለጥኩ በረርኩ… ወደጎተራዬ ዘልየ ገብቸ ድምፄን አጠፉሁ፡፡ መቼስ ጨለማውን ያየ እንደሆን ዓይን ቢወጉት እይታይም … ሊምረኝ መሰለህ? የታባቷ ገባች?” እያለ መርዝ እንደቀመሰ ውሻ ማሳው ውስጥ ተቅበዘዘ ወደ ጎተራው ሲቀርብ ቅጠሉ
ሊንኮሸኮሽ ይሰማኛል እስካሁንም በበር የሰው ኮቴ ስሰማ እጨነቃለሁ፡፡ እራቁቴን ነኝ፣
ብርዱ ተወው ፍርሐቱ ያንዘፈዝፈኛል… ኋላ በዱላው ጎተራውን መታ መታ ሲያደረገው
ይኼ የከረመ አቧረው እንደ ዝናብ ወረደብኝ… እሳልኩ… አቶ መናጢ! ነይ አትወጭም
እያለ ክዳኑን ሊከፍት ሲጀምር … ጎረቤቶች እሪታን ሰምተው ኡሮ እየተጯጯሁ ሲመጡ ሰማሁ በዛ በለሊት ጨለማ ውስጥ በዛች የጎተራ ሸቁር… ከሰዎቹ ላምባዲና የመጣች ቀጭን ጨረር ራቁት ገላዬ ላይ ስታርፍ እንደ ‘ጠሐይ የሞቀችኝ መሰለኝ
አቤት ደስታዋ አቤት! አቤት! አቤት! …አተረፉኝ፤ እሱንም በነጭ ለባሽ እያዳፉ ወደ ወሰዱበት እንጃ ልጆቹንም ወደ አክሰታቸን ዘንዳ ላኩን እዛው አደግን:ፍርሐቱ ግን ዛሬም ድረስ በርጋጊ አርጎኝ ቀረ! ቅጠል በተንኮሻኮሽ፣በበር የሚያልፍ ኮቴ በሰማሁ ቁጥር ብርክ ይይዘኛል እፈራለሁ ዘመኔ ያለቀው በፍርሐት ነው፡፡

ኑሮዬ እንደው መባከን ነው፤ እምብዛም ደስታ የለው… ከልጅነት እስከ እውቀት የሳኩባቸው፤ በደስታም የተጎበኘሁባቸው፣ ብርሃን ያየሁባቸው ቀናት ብቻ ነበሩ፡፡ ያ የሰባ ሰባት ርሃብ ስንቱን እንደ ቅጠል ያረገፈው መርገምት ማለፉን ያበሰረኝ
መንግሥትና ራዲዮኑ አይደለም፤ ብርሃን ነው ልጄ ብርሃን፡፡ ለሰው ብናገረው ውነት አይመስልም፡፡ ሰማዩ ሲደረቀበት የጥር ወር ፣ያለኝን አሟጥጫ ወዴት አባቴ ልሰደድ? እያልኩ ውጭ ላይ ከተፈጨበት ዓመት የሆነው የድንጋይ ወፍጮ ላይ ተቀምጨ ሳለቅስ ነበር፡፡ ጥር አሥር በአሥራ አንድ ማታ እንደ ነገ ብርሃነ ጥምቀቱ ሊከበር በዋዜማው ምሽት በዛ ኮከብ እንኳን በማይታይበት ጥቁር ሰማይ እንደ ፈትል ከር የቀጠነ ብርሃን ሰማዩን ለሁለት ሲከፍለው ደንግጬ በረገኩ፡፡ ያንን ሰማዩ ላይ ተዘርግቶ የጠፋ የብርሃን ዘንግ እንደገና አየዋለሁ ብዬ ባንጋጥጥ አልደገመውም ….በመነጋታው ምድሩ ላይ ጠፍቶ የኖረ ዝናብ ዶፍ ሆኖ ወረደ ከዝናቡም፣ ዝናቡ ካበቀለው ቡቃያም ይልቅ ያ የብርሃን ፀዳል ዓይኔ ላይ ዛሬም አለ .. ጥምቀት በመጣ ቁጥር ሰማዩ በብርሃን የተሞላ ይመስለኛል… የሕይዎቴን ትንሽ የምስራች እንዳቅሜ ልዘክር…አልጋ እስክይዝ ለጥምቀት ቀርቼ አላውቅም ነበር፡፡

ባልም እንደ አውሬ እያስፈራኝ ስሸሽ፣ ዘርም ሳላፈራ ኖርኩ አልከፋኝም! ቤቴን የምትሞላ ያች ጨረር የግዜር እጅ ነበረች … የግዜር ጣት !እዚህ ቤት ስንት ዓመቴ …?
ወደ ሃያ ዓመት ኖርኩ፤ ማስጠገን አቅቶኝ መሰለህ ልጄ? ዘጠኝ ዓመት ሙሉ አልጋ ላይ ስውል…የምትዳስሰኝ የግዜር ጣት እንዳትታጠፍ ብዬ.ያች ጨረሬን! ወስዳችኋት፡፡ ጨለማው እየቀረበ ነው፤የሰው እጅ በሰራት ብርሃን የማይገፈፍ ጨለማ እየመጣ ነው… ታውቆኛል ከእንግዲህ ብርሃን የለም፤ ተላመጅው ሲለኝ ነው መቃብሬን…?

Breaking News
Daily Feta Posts

Recent post

Ethiopian Movies

Other Post