ፌስበኩ የኩባንያውን ስም ወደ ሜታ መቀየር ለምን አስፈለገው?

“ጥቂት ሰዎች አሁን ስለወደፊታችን የምንጨነቅበት ጊዜ አይደለም እንደሚሉ አውቃለሁ፣ በአሁኑ ጊዜ መሰራት ያለባቸው አስፈላጊ ጉዳዮች እንዳሉም መቀበል እፈልጋለሁ፡፡ ደግሞም ሁሌም ይኖራሉ፡፡ ታዲያ ለበርካታ ሰዎች ስለወደፊቱ የሚያስቡበት አንዳች ጥሩ ጊዜ ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም፣ ነገር ግን ልክ የኔን አይነት ስሜት የሚያንፀባርቁ በርካታ ሰዎች እንደሚኖሩ ማወቅ አለባችሁ፡፡ እምንኖረው እየገነባን ያለነውን ነው፡፡ ስለዚህ ስህተት ስንሰራ እየተማርን፣ እየገነባን ወደፊት እንጓዛለን፡፡” ውድ የሰዋስው ቤተሰቦች ይህ የፌስቡክ መስራች ማርክ ዙከርበርክ ከተናገረው የተወሰደ ነው፡፡

ፌስቡክ የኩባንያ ስሙን ከፌስቡክ ወደ ሜታ መቀየሩ በይፋ እየተነገረ ይገኛል፡፡ ለምን?

 

 

የቀድሞ ሰራተኞቹ በርካታ ሚስጥራዊ መረጃዎችን አደባባይ ላይ በማስጣታቸው ፌስቡክ በርካታ ጊዜ ፍርድ ቤት ተመላልሷል፡፡ በሌላ ገጽ ደግሞ የተጠቃሚዎቼን መረጃ ለመርማሪዎች አሳልፌ አልሰጥም በማለቱ ከፌደራል የምርመራ ቢሮ(ኤፍቢአይ) ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ ሲገባ ማስተዋልም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡

በአለማችን ላይ እስከዛሬ በደንብ ከተሸጡ የንግድ ምልክቶች መካከል ቁንጮ ላይ የተቀመጠው ይህ ግዙፍ ኩባንያ የተጠቃሚዎችን መረጃ አያያዝም ላይ ዝርክር ነው እየተባለ ይታማል፡፡ ለማሳያ ያክል እንኳን በቅርቡ ለሰዓታት የተቋረጠበትን ክስተት ማስታወስ ይቻላል፡፡ ፌስቡክ በየወሩ በንቃት የሚጠቀሙትን ከ2.8 ቢሊዮን በላይ ተጠቃሚዎቹን መረጃ ጨምሮ ከዲኤንኤስ ሰርቭር ላይ ለሰዓታት ተሰውሮ ነበር፡፡ ወዲህ ቢባል ወዲያ ቢባል ዲኤንኤስ ሰርቨሩ ፌስቡክን አላውቀውም እያለ ተጠቃሚዎች ይይዙት ይጨብጡት አጥጠው ነበር፡፡ በጊዜው አንዳንድ ከኩባንያው ሾልከው ከሚወጡ ያልተረጋገጡ መረጃዎች በቀር ፌስቡክን የበላውን ጅብ አውቃለሁ በዚያ ሲጮህ ሰማሁት የሚል አልተገኘም ነበር፡፡ አንዳንድ መረጃዎች የሳይበር ጥቃት ደርሶበታል ሲሉ ሌሎች ደግሞ በሰርቨሮቹ ላይ ቴክኒካል ችግሮች ገጥሞታል በማለት ለማስተባበል ሲሞክሩ ታይተዋል፡፡

የኋላ የኋላ ግን ከሰዓታት ፍለጋ በኋላ ፌስቡክ ከተሰወረበት ሲገኝ ብቻውን አልነበረም የመጣው፣ ሌሎች ተጨማሪ ታሪኮችን ታቅፎ ነበር፡፡ በሰዓታት ልዩነት ወደ 7 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ኪሳራ ደረሰበት፡፡ እጅግ በርካታ የሚባሉ የተጠቃሚዎች መረጃዎች እንደተመዘበሩበት ታወቀ፡፡ አለም በፌስቡክ ላይ ያለውን አመኔታ ደርዝ ማስያዝ ጀመረ፡፡ ሌላ ጊዜ አንዳንድ ተጠቃሚዎች ለአመጽ የሚያነሳሱ፣ ግለሰባዊ መብትን የሚጥሱ፣ በአገራት ሉአላዊነት ላይ ጣልቃ የሚገቡ፣ በመንግስታት መካከል ግጭትን ሊቀሰቅሱ የሚችሉ መረጃዎች በገፁ ላይ ሲለጠፉ እንዳላየ ያልፋቸዋል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ዘራፍ ይላል፡፡

ለማሳያ እንኳን በቅርቡ የወጣ አንድ ጥናት እንዳሳየው ፌስቡክ በኢትዮጵያ ውስጥ ብጥብጥ እንደሚነሳ እያወቀ ድርጊቱን የሚያባብሱ መረጃዎች በተጠቃሚዎች ገጽ ላይ ሲለጠፉ ጆሮ ዳባ ልበስ አይኔን ግንባር ያድርገው ብሎ ማለፉን አሳብቀውበታል፡፡

አሁን አሁን የፌስቡክን ስም በመጥፎ የማያነሳ ሰው በየአለም አገራት ፈልጎ ማግኘት አይቻልም፡፡ ከአደጉ አገራት እስከ በማደግ ላይ ያሉ አገራት ሁሉም የየበኩላቸው ክስ አላቸው፡፡ ከታዋቂ ሰዎች እስከ ተራ ግለሰቦች ፌስቡክን የሚወዱትን ያክል የሚጠሉበትም ምክንያት አላቸው፡፡ እንደሌሎቹ የምዕራባዊያን አገራት ሚዲያዎች ሁሉ አንዳንዴ ፌስቡክ ሁሉን እኩል አያስተናግድም የሚሉ ተችዎች ብዙ ናቸው፡፡ ይህ ብዙዎች የሚያውቁት እውነታ ነው ፌስቡክም የተወሰነውን ሃሳብ ይጋራል፡፡

ማርክ ዙከርበርግ ግን እንዲህም ይላል “ዛሬ ዛሬ ሰዎች የሚመለከቱን ልክ እንደማህበራዊ አውታረ መረብ ብቻ ነው፡፡ አውቃለሁ ፌስቡክ በአለማችን ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የተሰራጨ አንድ የንግድ ምልክት ነው፡፡ ስለ አዲሱ ማንነታችን ስለ አዲሱ ምዕራፍ ብዙ ጊዜ አስቢያለሁ፡፡ በእኛ ዲኤንኤ ውስጥ ሰዎችን በቴክኖሎጂ የምናገናኝ ኩባንያ ነን፡፡ በስራችን እንደ ኢንስታግራም፣ ዋትሳፕ የመሳሰሉ ሌሎች የቴክኖሎጂ ድርጅቶች አሉን፡፡ አሁን የእነርሱን እናት ስም ከፌስቡክ ወደ ሜታ የምንቀይርበት ሰአቱ ነው፡፡”

በርግጥ ማርክ ስለ ኩባንያ ስያሜው ይህን ይበል እንጂ አንዳንዶች “ፌስቡኩ በቀድሞ ሰራተኞቹ አማካኝነት ከጉያው ያፈተለኩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሚስጥራዊ ሰነዶች ስሙን እንዳይሆን እንዳይሆን አድርገው ስላጠለሹበት የኩባንያውን ስም ለማደስ ሲባል ነው አዲስ የኩባንያ ስም ያስፈለገው” ይላሉ፡፡

ማርክ በበኩሉ “ስያሜው የኩባንያችንን የወደፊት ምኞት በሚገባ የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ ተጠቃሚዎች ደህንነታቸው መጠበቅ አለበት፡፡ ለተሳሳተ መረጃ መጋለጥ የለባቸውም፤ እንዲሁም ወደፊት ተጠቃሚዎች ከእውነተኛው አለም ጋር በምናባዊ እውነታዎች እንዲገናኙ የሚያደርጉ ቴክሎጂዎችን በኩባንያችን ላይ በማካተት አዲስ የኦንላይን ግዛቶችን መፍጠራችን ስለማይቀር ሜታቨርስ ላይ በስፋት ስለምንሰራ፣ በርከት ያሉ የቴክኖሎጂ አገልግሎቶችን የሚይዝ መጠሪያ ግድ ስላለን የስያሜ ለውጡ አስፈልጎናል፡፡” ይለናል፡፡

ውድ የሰዋስው ቤተሰቦች በነገራችን ላይ ሜታቨርስ ማለት ሰዎች አምሳያዎችን በመጠቀም በዲጂታል መንገድ መስተጋብር የሚፈጥሩበት ምናባዊ ቦታ ነው። ይህ ደግሞ እንደማርክ እሳቤ ከሆነ ወደፊት ሰዎች የፌስቡክ ኩባንያ አገልግሎቶችን ለመጠቀም የግድ የፌስቡክ ተጠቃሚ መሆን ላያስፈልጋቸው የሚችልበትን አሰራር ይዞ ይመጣል ማለት ነው፡፡

Celebrity News
Daily Feta Posts

Recent post