የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ሮሮና የከተማው ትራንስፖርት ቢሮ መልስ !

ነዳጅ ጨምሯል በሚል መንግሥት ካስቀመጠው ታሪፍ ውጪ ከ10 ብር እስከ 15 ብር ጭማሪ እየተደረገብን ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያነጋገራቸው የትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ተናገሩ። የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ በበኩሉ ችግሩን በ90 ቀናት ውስጥ ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል። መገናኛ አካባቢ ትራንስፖርት ለማግኘት ተሰልፈው ያገኘናቸው ወይዘሮ አልማዝ ከበደ እንደተናገሩት፤ መንግሥት በነዳጅ ታሪፍ ላይ የዋጋ ማሻሻያ ካደረገ ማግስት ጀምሮ አብዛኞቹ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች በራሳች ፍላጎት ከ10 እስከ 15 ብር የዋጋ ጭማሪ እያደረጉ ነው። ነዳጅ ጨምሯል በሚል ሰበብ በቀን 10 እና 15 ብር እንዲሁም ምሽት ላይ እስከ 20 ብር ጭማሪ የሚያስከፍሉ ታክሲዎች መኖራቸውን የገለጹት ወ/ሮ አልማዝ፤ ይህንንም ህገወጥ አካሄድ ለመቆጣጠር የሚደረግ ጥረት አለመኖሩን እንደታዘቡ ተናግረዋል።

አብዛኛው ተሳፋሪም ህገወጥ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች በሚያስቀምጡለት ታሪፍ መሰረት እንደሚከፍል፤ ተሳፋሪው መብቱን ለማስከበር ጥረት አለማድረጉ ችግሩን እያባባሰው መሆኑንም ጠቁመዋል።

መንግሥት ካስቀመጠው ታሪፍ በላይ ተሳፋሪን አስገድዶ ከመጫን ባሻገርም በተለይ ህዝብ በሚበዛባቸውና የትራንስፖርት እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች እየቆራረጡ መጫን በስፋት እንደሚታይ ተናግረዋል። ሌላኛው የትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚ አቶ ነጋሽ ተክሉ በበኩላቸው፤ ከመገናኛ አባዶ መስመር በተለይ ድጋፍ ሰጪ አውቶቡሶች በሙሉ አቅማቸው እየሰሩ አይደለም ብለዋል።

ምሽት ላይም የትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች የማይገኙ በመሆኑም አሽከርካሪዎች ከታሪፍ በላይ በተጋነነ ዋጋ እንደሚጭኑ ተናግረዋል። የሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎችም ስምሪቱንና የህብረተሰቡን ችግር ወርደው በማየት ቁጥጥር ሊያደርጉ እንደሚገባም አመላክተዋል።

ወይዘሮ ቤተልሔም አደመ የተባሉ የትራንስፖርት ተጠቃሚ በበኩላቸው፤ ከቦሌ አስኮ ወይም ከሳንሱሲ ወደ ቦሌ የሚመጡ የአንበሳ አውቶቡሶች ተጠባብቀው በተከታታይ የሚሄዱ እና በሰዓታቸው የማይመጡ በመሆኑ ተሳፋሪው ለእንግልት መጋለጡን ይናገራሉ።

ከመገናኛ ወሰን አካባቢም የታክሲ አገልግሎት ምሽት ላይ አምስት ብር የነበረው በአሥር ብር እንደሚጫን ገልጸዋል። በታፔላ የማይሰሩ ተሽከርካሪዎችም በርካታ እንደሆኑ ጨምረው ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ በበኩሉ፤ በተሳፋሪዎቹ የሚነሱት ቅሬታዎች እውነትነት እንዳላቸው ገልጾ፤ ችግሩን ለመቅረፍ በቀጣዮቹ 90 ቀናት እቅድ ተነድፎለት ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግ መሆኑን አሳውቋል።

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ እፀገነት አበበ የህዝብ ትራንስፖርት ፍላጎትና የህዝብ ተሽከርካሪ አቅርቦት የተመጣጠነ ባይሆንም ባሉት ተሽከርካሪዎች አቅምን አሟጦ ለመጠቀም ቢሮው የስምሪት እና የቁጥጥር ስርዓቱን አጠናክሮ ይሰራል ብለዋል።

ታፔላ የሚደብቁ፣ በፈለጉበት መስመር የሚያቆራርጡ፣ ያልተገባ የክፍያ አገልግሎት የሚጠይቁ የታክሲ አሽከርካሪዎች እንዳሉና ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት በቀጣይ ጥብቅ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጠዋት፣ ማታ፣ የምሽት የቀን የሚባል የተለያየ ታሪፍ እስከሌለ ድረስ በተቀመጠው ታሪፍ ብቻ እና ብቻ አገልግሎት ሊሰጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በታክሲ አሽከርካሪዎች በኩል የሚቀርበው የታሪፍ ማስተካከያ ጥያቄን በተመለከተም በጥናት ምላሽ እስከሚሰጥ ድረስ ታሪፍ ጨምሮ ማስከፈል የሚያስጠይቅ በመሆኑ በተቀመጠው ታሪፍ አገልግሎት እየሰጡ ለጥያቄያቸው መልስ እስኪሰጥ ድረስ ህግን ጠብቆ መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል።

የትራንስፖርት እጥረቱንም ለማቃለል የከተማ አስተዳደሩ በቅርቡ 110 አውቶቡሶች ለማስገባት በሂደት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

(የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)

Celebrity News
Daily Feta Posts

Recent post

Daily Feta

Other Post